
የፋሲል እና ባሕር ዳር ከነማ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኞች በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ የመጀመሪያ ምዕራፍ ካሁኑ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚቀርቡ ገለፁ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 01/2013 ዓ.ም (አብመድ) የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ አዲስ አበባ ላይ የነበረውን ቆይታ አጠናቆ ወደ ቀጣዩ የውድድር ቦታ ጅማ ከተማ አቀንቷል፡፡ አዲስ አበባ ላይ እስከ ስድስተኛ ሳምንት ድረስ የነበረውን መርሃ ግብር አከናውኗል፡፡
ፋሲል ከነማ 13 ነጥብ በመሰብሰብ በግብ ክፍያ በሀድያ ሆሳዕና ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ የአዲስ አበባ ቆይታውን አጠናቋል፡፡
ባሕር ዳር ከነማ ደግሞ በ10 ነጥብ አራተኛ ደረጃን በመያዝ ወደ ጅማ ከተማ አምርቷል፡፡ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች በአዲስ አበባ የነበራቸውን ቆይታ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት አጋርተዋል፡፡
የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በጨዋታ አጀማመራችን ተጋጣሚ ቡድንን ጫና ውስጥ በመክተት ግብ ለማስቆጠር ስናደርግ የነበረው እንቅስቃሴ መልካም ነበር ብለዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ቡና እና ከባሕር ዳር ከነማ ጋር በነበራቸው ጨዋታ የተጫዋቾች ብልጫን መጠቀም አለመቻላቸው እና ወጥ የሆነ የቡድን መንፈስ ማጣታቸው በአዲስ አበባ ቆይታቸው የታየ ክፍተት እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
ቡድናቸው በሚፈልጉት መልኩ እንዳልተጫወተላቸው የተናገሩት የባሕር ዳር ከነማው አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እንደ ቡድን ለመጫወት፣ እያንዳንዱን ጨዋታ ለማሸነፍ የነበራቸው ተነሳሽነት እና ልምምድ ላይ ያጠኑትን የጨዋታ ስልት ሜዳ ውስጥ ለመተግበር ያደርጉት የነበረው ሙከራ የቡድናቸው በጎ ጎን እንደነበር አንስተዋል፡፡
አሰልጣኝ ፋሲል በአዲስ አበባ ቆይታቸው የቡድናቸው የማጥቃት እንቅስቃሴ እና አቅም ደግሞ በሚፈለገው ልክ አለመምጣቱ ክፍተታቸው እንደነበረ ተናግረዋል፡፡
የሁለቱም ክለብ አሰልጣኞች የታዩባቸውን ክፍተቶች አርመው ጅማ ከተማ ላይ ካሁኑ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚቀርቡ ገልጸዋል፡፡
የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ ከሰባተኛ እስከ አስራ አንደኛ ሳምንት ያለውን ሁለተኛ የውድድር ምዕራፍ በጅማ ከተማ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ያከናውናል፡፡ ሥስተኛው ምዕራፍ የውድድር ጊዜ ደግሞ ባሕር ዳር ከተማ ላይ ይካሄዳል፡፡
ዘጋቢ፡- ንዋይ ሙሉጌታ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ