
የፕሬዝዳንት ትራምፕ ደጋፊዎች የመንግሥት መቀመጫና የሁለቱ ምክር ቤቶች አዳራሾች የሚገኙበትን ካፒቶል ሒልን ጥሰው መግባታቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ድርጊቱን በማውገዝ ላስተላለፉት መልዕክት ምስጋና ቀረበ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 30/2013 ዓ.ም (አብመድ) በዋሽንግተን ዲሲ የአሜሪካ መንግሥት መቀመጫ በሆነው የካፒቶል ሒል ግዙፍ ህንጻ ላይ የትራምፕ ደጋፊዎች ወረራ ፈጽመው ለሰዓታት ግርግር ተፈጥሮ ነበር።
ድርጊቱን ጆ ባይደን “በአሜሪካ ዲሞክራሲ ላይ ጥቃት ተሰንዝሯል” ሲሉ ነበር የገለጹት፡፡
ካፒቶል ሒል የአሜሪካ መንግሥት መቀመጫ ሲሆን የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት የሚገኝበት፣ በርካታ ቢሮዎች ያሉበት ታሪካዊ ሕንጻ ነው።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሬይነር ድርጊቱን በርካታ ኢትዮጵያውያን ማውገዛቸውን እና ከአሜሪካ መንግሥት ጎን መሆናቸውን በተመለከተ ላስተላለፉት መልዕክት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አምባሳደሩ የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስ በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን የምርጫ ኮሌጅ ድምጽ አጠናቆ የጆ ባይደን እና የካማላ ሃሪስን መመረጥ አረጋግጧል ብለዋል፡፡ (እአአ) ጥር 20/2021 ቃለ መሃላ እንደሚፈጽሙ እና ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንደሚከናወን አምባሳደሩ አስታውቀዋል፡፡
‹‹ትናንት በዲሞክራሲያችን ላይ የኃይል እና አመፅ ድርጊት የፈጸሙ ወንጀለኞች በአሜሪካ የሕግ የበላይነት በጠበቀ መልኩ ተጠያቂ ይሆናሉ›› ብለዋል፡፡
አምባሳደር ማይክ ሬይነር በነበረው አስቸጋሪ ሁኔታ ለአሜሪካ መንግሥት የድጋፍ መልዕክቶችን ለላኩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከልብ የመነጨ ምስጋናም አቅርበዋል፡፡
በአሜሪካ እና በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ያለው ዘላቂ ወዳጅነት እና አጋርነት ቀጣይ እና የበለፀገ እንደሚሆን አምባሳደሩ ጠቁመዋል፡፡
ምንጭ፡-በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ
በየማነብርሃን ጌታቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ