
በአፍሪካ የጋራ የነፃ ገበያ መመስረት የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ፣ ግሽበትን ለመቀነስ እና የእውቀት ሽግግር እንዲስፋፋ ለማድረግ እንደሚረዳ ተገለፀ።
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 30/2013 ዓ.ም (አብመድ) በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር ደመላሽ ሀብቴ እንዳሉት በአፍሪካ ሀገራት መካከል የተቀናጀ የኢኮኖሚ ግንኙነት ባለመኖሩ አህጉሪቱ ከ80 በመቶ በላይ የንግድ እንቅስቃሴዎች እያደረገች ያለችው ከአውሮፓ፣አሜሪካና እስያ ሀገራት ጥገኛ በመሆን ነው። በዚህም የተነሳ አህጉሪቱ ደካማ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ፣ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የሚከሰትባትና ዝቅተኛ የእውቀት ሽግግር የሚስተዋልባት ሆና ቆይታለች ብለዋል።
የአፍሪካ ሀገራት ካሁን ቀደም እርስ በእርስ ያላቸውን የንግድ ትስስር ለማሳደግ ጅምሮች ቢኖሩም ውጤታማ ባለመሆናቸው እስካሁን እርስ በእርስ ያላቸው ግንኙነት ከ20 በመቶ የዘለለ አልነበረም ያሉት ዶክተር ደመላሽ፤ በተመሳሳይ ደረጃ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችንም ሆነ እንደ ነዳጅ ያሉ ያለቀላቸው ምርቶች በአፍሪካ ሀገራት ውስጥ በስፋት እየተመረቱ ቢሆንም ሌሎች ተጠቃሚ ጎረቤት ሀገራት የሚያስገቡት ካደጉት ሀገራት መሆኑን ተናግረዋል።
በአህጉሪቱ የተጠናከረ የንግድ ልውውጥና የዳበረ የነፃ ገበያ ተፈጥሮ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው የተቀላጠፈ እንዲሆንና በሚጠበቀው ደረጃ እንዲያድግ የአፍሪካ ሀገራት የንግድ ልውውጥ በጋራ ነፃ ገበያ ሊጠናከርና ሊስፋፋ ይገባዋል ብለዋል።
የአፍሪካ የጋራ የነፃ ገበያ መመስረትና ወደተግባር መግባት አፍሪካ እንደ አህጉር ከሌላው ዓለም ጋር ለሚኖራት የንግድና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች በር የሚከፍት እንደሚሆንም አመልክተዋል።
ነፃ ገበያው በአሁኑ ወቅት በስፋት የሚታየውን ወደ መካከለኛው ምሥራቅና ሌሎች ሀገራት የሚደረገውን የሰው ኃይል ፍልሰት ወደ አፍሪካ እንዲሆን ያግዛል ያሉት ዶክተር ደመላሽ፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የእውቀት ሽግግሩም በየደረጃው የተቀላጠፈ እንዲሆን ይረዳል፤ በሀገራት መካከል የሚኖረውም የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተጠናከረ እንዲሆን ይረዳል ነው ያሉት።
የአፍሪካ የጋራ የነፃ ገበያ ትስስር በጥንቃቄ እየተቆጣጠሩ መሥራት፣ ትልልቅ ተቋማትን መገንባትና ጥራት ያላቸውን ምርቶች በማምረት ለጠንካራ ውድድር መዘጋጀት ከተቻለ እያንዳንዱ የአፍሪካ ሀገር ተጠቃሚ እንደሚሆን ዶክተር ደመላሽ መናገራቸውን ኢትዮ ፕረስ ዘግቧል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ