
<< ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ>>
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 29/2013 ዓ.ም (አብመድ) የሰው ልጆች ቤዛቸውን ጠበቁት፣ ናፈቁት፣ ተስፋ ጣሉበት፣ ተወልዶ እስኪታደጋቸው ድረስ በጨለማ ውስጥ ሆነው አሰቡት። ጥፋተኞቹም እነርሱ ሆነው ሳሉ ካሳ የሚከፍለው ግን እርሱ ሆነ። ዘመን እንደ ወራጅ ውኃ እያለፈ ሄደ። በፈጣሪ የዘመን አቆጣጠር አጭር፣ በሰው የዘመን አቆጣጠር ግን የብዙ ብዙ የሆነው ዘመን የሰውን ልጆች በጨለማ ጥሎ አለፈ።
ታላቁን ፍጡር ከገነት ያስወጣው ሰይጣን በሲዖል እንዳሻው እየሆነ ነበር። የሲዖል ደጆች እንደተከፈቱ የገነት ደጆች ደግሞ እንደተዘጉ የሚቀር መስሎት ነበር። እውነት የዘገዬ መሰለ። ግን እንደማይቀር ተስፋ ተጥሎበታል። የጨለማው ዘመን ሊጠናቀቅ የሲዖል ደጆች ሊዘጉ የገነት ደጆች ሊከፈቱ፣ ሰይጣን ከነጭፍሮቹ ተስፋ ወደሌለው እሳት ሊጣል ዘመኑ እየቀረበ ሄደ። የሰው ልጆች በእሳት ሆነው መልካምን ያስቡ ነበር። ተስፋ አላቸውና። ሰይጣን ግን በእሳት ውስጥ እሳትን ያስባል እንጂ ገነትን አያስብም። ተስፋ የለውምና።
የቅጣተኞች መኖሪያ የሆነችው ምድር ልትቀደስ፣ የደስታ ማዕበል በዓለሙ ሁሉ ሊፈስ፣ ጨለማው ተገፎ ብርሃን ሊወጣ ሲል ክርስቶስ በማይመረመር ጥበብ ሰው ሆነ። በአፈጣጠር ከሰው ወገን የሆነች፣ በአኗኗር ግን ሰማያዊት የሆነች፣ ከሀጥያት የነጣች፣ በልቧም፣ በሀሳቧም በምግባሯም መልካም የምታስብ ሰውን እና መላዕክትን፣ ሰውና እግዚአብሔርን፣ ምድርና ሰማይን የምታስታርቅ እመቤት በምድር ተገኘች።
ራሱን ሰጥቶ ምድርን ለማዳን የወደደው አምላክ በዚያች ንፅሒት ላይ አደረ። ዘር ሳይቀደመው፣ ምንም ሳይጨመርበት፣ በራሱ ጥበብ ሰው ሆነ። በሰውነቱ ሰውን አዳነ። ከሁሉም በላይ የሆነ ጠቢብ አመጣጡ አስደመመ። እፁብ ነህ ከማለት የዘለለ ማድነቂያ አንደበት፣ መመርመሪያ ብሰለት ጠፋ።
ክርስቶስ የነቢያት ትንቢት ይፈፀም ዘንድ በሀገረ እስራኤል በቤተልሔም ተወለደ። ምድራዊም ሰማያዊውም መንግሥት የእርሱ ሆኖ ሳለ፣ ለክበሩ መላእክት የሚሰግዱለት፣ ሳያቋርጡ ቅዱስ ቅዱስ የሚሉት፣ ሁሉም የሚደረግለት፣ ሁሉም የሚታዘዝለት ሆኖ ሳለ ለትህትና ሲል በከብቶች በረት ተወለደ። ከብቶች አሞቁት፣ እልፍ አዕላፍ መላእክት ጌታቸውን አመሰገኑት። የዓለም ቤዛ ተወልዷል አሉ። መላእክት ከሰማይ ሰባ ሰገል ከምድር ቤተሌሔም በደስታ ተናጠች።
ጨለማው ተገፈፈ የማይጠልቀው ፀሐይ ወጣ። ቤዛ ኩሉ ዓለም ተወልዷል አሉ። ክርስቶስ ሲወለድ የመላእክት እና የሰው ምስጋና ዛሬም ድረስ የልደቱ ቀን በታሰበ ጊዜ ይዘመራል። <<ቤዛ ኩሉ>> የሁሉ ቤዛ ይሉታል። ይህ ቃል የክርስቶስ የልደት ቀን በታሰበበት አብያተክርስቲያናት እና ገዳማት ሁሉ ቢባልም በደብረ ሮሐ ቅዱስ ላል ይበላ ግን ሥርዓቱ ለዬት ይላል። የምድራዊትና ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ተምሳሌት በሆነው የቅዱስ ላል ይበላ አብያተ ክርስቲያን የቤተልሔሙን ምስጋና በሚያስታውስ መልኩ ይፈፀማል።
ንጉሥ ወ ቅዱስ አናፄ መቅደስ ላል ይበላ ሥራውን በምክንያት ጀመረ በምክንያት አጠናቀቀ። ለቤዛ ኩሉ ስርዓት ትሆን ዘንድ የተመቼች ቤተክርስቲያንም አነፀ። እርሷም ከምድራዊት ኢየሩሳሌም ተምሳሌት ከሆኑት አንደኛዋ ቤተ ማርያም ናት። ቤዛ ኩሉ በቤተ ማርያም ይከወናል። ስርዓቱም፣ ልደቱ ከተበሰረ፣ ቅዳሴው ከተቀደሰ፣ ስጋውና ደሙ ከተፈተተ በኋላ ይደረጋል። በዚህች ቤተክርስቲያን ከሰማይ የወረዱትን መላእክት ከምድር የሄዱትን ኖሎት ሰባ ሰገልን በሚያስታውስ መልኩ ሥርዓቱ ይፈፀማል።
የቅዱስ ላል ይበለ አብያተ ክርስቲያናት ካሕናት ገሚሶቹ ጥበብ በጥቁር ካባ አድርገው፣ ገሚሶቹ ደግሞ ሸማ ወይም ጃኖ አድርገው በረድፍ ይሰለፋሉ። በቤተክርስቲያኗ ዙሪያ በጥበብ በተሰራውና ማሜ ጋራ እየተባለ በሚጠራው ጋራ ይሆናሉ። እነዚህ ክርስቶስ በቤተልሔም ሲወለድ ከሰማይ የወረዱት መላዕክት ምሳሌዎች ናቸው። ከጋራው ሥር ሆነው ምሥጋና የሚያቀርቡት ደግሞ በኖሎት በሰባ ሰገል ይመሰላሉ። ጥቁር ካባ በጥበብ የሚለብሱት ትልልቅ አባቶች እና መምህራን የሆኑት ናቸው። ሸማ ብቻውን የሚያደርጉት ደግሞ በእድሜያቸው አነስ ያሉ መሆናቸውንም አባቶች ነግረውናል።
<<ክርስቶስ መጽዐ ኀቤኔ ውስተ ማኅፀን ድንግር ኀደረ>> ክርስቶስ ወደ ዓለም መጥቶ በድንግል ማኅፀን አደረ ይላሉ። እልልታው ይቀልጣል። ደስታ ይሆናል። ቤተልሔም ዛሬ የሆነች ትመስላለች። ማሜ ጋራ ላይ ሶስት ጊዜ << ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ>> እያሉ ሰግደው ከስር ላሉት ይሰጣሉ ከስር ያሉትም እንደነርሱ ብለው ሰግደው ለላይኞቹ ይሰጣሉ። በዚህ ጊዜ ምዕመናን እልል ይላሉ፣ ካህናት ያዜማሉ ቅድስቲቷ ምድር በደስታ ባሕር ትሰጥማለች። ቤዛ ኩሉ ሀይማኖታዊ ስርዓት ሰውና መላእክት በጋራ <<ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብ>> እያሉ የሚያመሰግኑበት ነው። ምዕምናን ስርዓቱን ይናፍቁታል፣ ወደው ያዩታል፣ አምነው ያመሰግኑበታል።
ይህንን ሃይማኖታዊ ስርዓት በማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ ሥራዎች እንደተጀመሩ የላል ይበላ ከተማ አስተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መሪጌታ መልካሙ ዓለሙ ነግረውናል። ስርዓቱ እንደሚመዘገብ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡
እንኳን አደረሳችሁ።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ