
“በእምዬ ምኒልክ በከበረው ንጉሥ፣
በኃይለስላሴ በከበረው ንጉሥ፣
ጤፉን በልተህ እንደሁ መቋጠሪያ መልስ”
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 29/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአንኮበር ወረዳ ሃይማኖታዊ በዓላት በልዩ ልዩ ባሕላዊ ክዋኔዎች ይደምቃሉ። ከነዚህ መካከል የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ጥንግ በሚባል ጨዋታ ይደምቃል።
የጥንግ ባህላዊ ጨዋታ በአንኮበር ወረዳ በስፋት የሚከወን የወንዶች ጨዋታ ነው። ይህ ባህላዊ ጨዋታ ከገና እስከ ጥር 21 ባሉት ሃይማኖታዊ በዓላት በተለዬ ድምቀት ይከበራል። በጨዋታው የሚሳተፉት ሰዎች አካባቢውን መሰረት ያደረገ ወሰን በመሰየም የሚጫወቱ ሲሆን ለጨዋታው ህግ ተገዥ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ኳስ ወይም ጥንግ፣ ለጊ (የቡድን አባት)፣ ተጨዋች (ቀላቢ) እና ዳኞች ይኖሩታል፡፡
ጨዋታው ሲጀመር የአንደኛው ቡድን አባት ወይም ጥንግ ለጊ ማሻማት ይጀምራል። የተሻማውን ኳስ የያዘው ቡድን አባት ይቀጥላል። እስከተቀመጠው ወሰን ድረስ ግብ ለማስቆጠር ጨዋታው ይቀጥላል። የሚያሸንፈው ቡድን “ኦሆ ያ ሆዬ” በማለት በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት የፈጸሙ አካላትን ያወግዛሉ። ውግዘቱን ወይንም ኩነኔውን አሸናፊም ተሸናፊም እየተቀባበሉ ሞቅ ያደርጉታል።
በገና ጨዋታ ከሚወገዙ ሰዎች መካከል በስርቆት በተሰማራ ግለሰብ ወይም ቡድን ላይ የሚደረገው ዘመቻ ሰፊውን ድርሻ ይወስዳል።
“በእምዬ ምኒልክ በከበረው ንጉስ፣
በኃይለስላሴ በከበረው ንጉስ፣
ጤፉን በልተህ እንደሁ መቋጠሪያ መልስ” ይላል አርሶ አደሩ ምርቱ ከተሰረቀበት ቢያንስ ምርቱ የተቋጠረበትን ማዳበሪያ ለሌላ ምርት እንዲሆነው ይመልስለት ዘንድ በመማፀን።
“የሌባ መቃብር መች እንደዚህ ነበር፣
ከታች አጋም እሾህ ከላይ ግራር ነበር
የሌባ ምልክቱ አጭር ነው ቁመቱ፣
ጠባብ ከደረቱ ከውሃ ዳር ቤቱ፣
ጨጓራ ለማጠብ እንዲመቻት ሚስቱ፣
ጫማውን ሲገዛ ነግዶ ነው ብዬ፣
ቤቱንም ሲሠራ አምርቶ ነው ብዬ፣
ለካስ ሰርቆ ኖሯል እከድ እከድዬ” በማለት ሌባውን ለማስተዋወቅ ሊገልፀው የሚችል ማሳያ ያቀርባሉ። ታዲያ በዚህ ጊዜ ድንገት ሌባው ያልታወቀ መስሎት ከተጨዋቾች ውስጥ ከተገኘ ያሳፍሩታል።
“የምን ቀየጥ ቀየጥ እንደ ንፍሮ እህል፣
የፍየሏ ሌባ ውጣ ከመሃል” በማለት ያሸማቅቁታል።
ሌባው ሳይገኝ ቀርቶ ወዳጆቹ ካሉም
“አንኮበር ተንዶ ተይዟል በገመድ፣
ከፊቱ ከብዶታል የነሌቦ ዘመድ” በማለት ሌባውን ባያገኙ እንኳን የቅርብ ወዳጆቹን ይወርፋሉ። ይህም የሌባው ዳፋ በንጹሓን ወዳጆቹ ላይ እንኳን ሳይቀር እንደሚያርፍ ማሳያ ነው።
የሙስናን አስፀያፊነትና የስነ ምግባር ብልሽት አጥብቀው ይቃወማሉ፤ ያወግዛሉ፡፡ በድርጊቱ የተሳተፉትንም በግጥም ይኮንናሉ። በባሕላዊ ጨዋታው ስንፍና ይወገዛል። ምክንያቱም ለአንድ ሀገር እድገትና ስልጣኔ ዋንኛ እንቅፋት በመሆኑ።
“እንዝርቱም ወደቀ ማን ይፍተልበት፣
ደጋኑም ወደቀ ማን ይንደፍንበት፣
ለመገዣ እንኳን ጠፋ ልቃቂት፣
ማረስ አይበልጥም ወይ በንሺ በንሺ፣
እሰው ማሳ ገብቶ ከማንኮሻኮሽ” በማለት እንዴት መሥራት እንዳለበት ምክር አዘል ስንኝ ይቋጥሩለታል።
በገና ጨዋታ መጥፎ ሥራ የሠራ ብቻ አይወገዝም፣ መልካም ሥራ የሠራ የማኅበረሰቡ አርዓያም እውቅና ይሰጣል፤ ይመረቃል፤ እንዲበረታታ ይሞገሳል። ይህ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ስነቃል በአንኮበር ወረዳ በስፋት የሚከወን መሆኑን ከወረዳው ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ይህንን ባህል እውቅና ሰጥቶ ለቱሪዝም ጥቅም በማዋል በኩል የአስፈላጊነቱን ያህል እንዳልተሠራበት በጽሕፈት ቤቱ የባሕል እሴቶች ኢንዱስትሪ እና ልማት ቡድን መሪ የኋላወርቅ ታደሰ ነግረውናል። ባሕሉን በስፋት ለማስተዋወቅ በአሁኑ ወቅት በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ