‹‹ድርጊቱ የታላቋን አሜሪካ ክብር የማይመጥን አሳፋሪ ተግባር ነው›› የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን

187
‹‹ድርጊቱ የታላቋን አሜሪካ ክብር የማይመጥን አሳፋሪ ተግባር ነው›› የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 29/2013 ዓ.ም(አብመድ) የጆርጂያ ግዛት እንደራሴዎች ምርጫ በዲሞክራቶች የበላይነት ተጠናቋል። ይህ ያልተዋጠላቸው የትራምፕ ደጋፊ ናቸው የተባሉ አሜሪካዊያንም ኮንግረስ ካፒቶል ሂል በተባለው ግቢ ውስጥ በኃይል በመግባት ታሪካቸውን የማይመጥን የተባለለትን አመፅ ፈፅመዋል፡፡
‹‹ሁለተኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው የጆርጂያ ግዛት እንደራሴዎች ምርጫ በዲሞክራቶች የበላይነት ተጠናቋል። ተወካዮቹ ሚስተር ዋርኖክ እና ሚስተር ኦሶፍም አሸንፈዋል። ሁለቱ እጩዎች በቀጥታ የሴኔት አባል መሆናቸውን ተከትሎም ሪፐብሊካኖች በላዕላይ ምክር ቤት ውስጥ የነበራቸውን የበላይነት አጥተዋል። የሪፐብሊካን እጩ ኬሊ ሊዮፍለርን እና ዴቪድ ፐርዲዩን የተሸነፉት በጠባብ ልዩነት ነው።
በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ውስጥ የዲሞክራቶችና የሪፐብሊካኖች ውክልና ሆኗል። ቀሪው የከፍተኛው ምክር ቤቱን ሸንጎ የሚመሩት ተመራጯ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሜላ ሐሪስ የሚሰጡት ድምፅ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራፕ ደጋፊዎች ናቸው የተባሉ አሜሪካዊያን ኮንግረስ ካፒቶል ሂል ውስጥ በኃይል በመግባት አመፅ አካሂደዋል፡፡ የፀጥታ አካላት ብዙ ጉዳት ሳይደርስ ችግሩን ለመቆጣጠር ተንቀሳቅሰዋል ቢባልም የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ እና የኮንግረስ አባላት ለደኅንነታቸው ሲባል ወደ ሌላ ቦታ መወሰዳቸውም እየተነገረ ነው።
የአማፂያኑን ድርጊት የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን ጨምሮ በርካቶች እያወገዙት ይገኛሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ‹‹ድርጊቱ የታላቋን ሀገር ክብር የማይመጥን አሳፋሪ ተግባር›› ሲሉ ተችተውታል። አሜሪካዊያን በሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ሊያምኑ ይገባል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
በታዘብ አራጋው
ምንጭ፡- ቢቢሲ እና አልጀዚራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየልደት በዓል በታቦር ተራራ!
Next articleከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከጦር አካል ጉዳተኞች ጋር የልደት በዓልን እያከበሩ ነው፡፡