የልደት በዓል በታቦር ተራራ!

276
የልደት በዓል በታቦር ተራራ!
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 29/2013 ዓ.ም (አብመድ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ክርስቲያኖች 2 ሺህ 12 ዓመታትን በሃሳብ ወደ ኋላ ተመልሰው በቤተልሄም በከብቶች ግርግም ውስጥ የክርስቶስን መወለድ በደስታ እያሰቡ ያከብራሉ፡፡
የክርስቶስ ልደት በክርስቲያኖች ዘንድ በትልቅ ጉጉት ይጠበቃል፤ በደስታም ይከበራል፡፡ ምክንያቱም ዕለቱ የነቢያት ምኞት፣ የመልአክት ውዳሴ፣ የእረኞች ህብረ ዝማሬ፣ የሰው ልጆች የመዳን ብስራት እና የሰብዓሰገል ስግደት ምክንያት የሆነው የክርስቶስ ልደት ነውና፡፡ በዚያች ሌሊት እሳት እየሞቁ መንጋቸውን ለሚጠብቁ እረኞች መላዕክት ‹‹በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን በምድርም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ሰዎች ሰላም ይሁን›› ብለው እየዘመሩ የክርስቶስ መምጣት ስለ ሰላም መሆኑን ያበስራሉ፡፡
በነቢያት ትንቢት የተነገረለት የሰው ልጆች የመዳን ተሰፋ የሆነው የክርስቶስ ልደት በኢትዮጵያ አከባበሩ የተለየ ድባብ አለው፡፡ በተለይ በታቦር ተራራ ድምቀቱ ልዩ ነው፡፡ 2 ሺህ 706 ጫማ ከፍታ ባለው ቦታ በአፄ ሰይፈ አርድ ዘመነ ንግስና (1344-1372) እንደተመሰረተች በሚነገርላት የተራራዋ ከተማ ደብረ ታቦር ከከፍታዋ በላይ ባለ ከፍታ አንድ ልዑለ አድባራት ይገኛል፡፡ በታቦር ተራራ ላይ የተመሰረተው ደብረ ታቦር ኢየሱስ በንጉሠ ነገስት ዳግማዊ ቴዎድሮስ የተመሰረተ እና ከግብፅ ሃገር በመጡ አራት ጳጳሳት ተባርኮ አገልግሎት እንደጀመረ ይነገርለታል፡፡
የልደት በዓል በደብረ ታቦር ተራራ በተለየ ድባብ የሚከበር በዓል ነው፡፡ ከጉና ወዲያ ማዶ እስከ ቤተልሄም እና ከጥጥራ አሻጋሪ እስከ ጣራ በአራቱም አቅጣጫ ላል ይበላ ያልሄዱ ምዕመናን መጥተው በታቦር ተራራ ላይ ልደትን ያከብራሉ፡፡ ዳገቱን ወጥተው እና ብርዱን ችለው ከደብረ ታቦር አናት ላይ የሚሰባሰቡት አማኞች የክርስቶስን የልደት ምሽት እንደ ጎለጎታ በዝማሬ፣ በሽብሸባ ያደምቁታል፡፡ በምሽቱ የጧፍ እና ሻማ ብርሃን እንደሰማይ ከዋክብት ደምቆ ይስተዋላል፡፡ የልደት በዓል በደብረ ታቦር ካህናት በቅዳሴ፤ ዲያቆናት በውዳሴ፣ መምህራን በስብከት፤ አባቶች በፀሎት እንዲሁም ወጣቶች በእምቢልታ ልጃገረዶች በእልልታ ከምሽት እስከ ንጋት ይዘልቃል፡፡
የበረቱት በቤተ ክርስቲያኑ ግቢ ውስጥ አድረው ያልቻሉት ዶሮ ሲጮኽ ዘልቀው ቅዳሴው ረፋዱ ላይ ይጠናቀቃል፡፡ የአጥቢያው ሰዎች በጠዋት አርደው እና ምግብ አዘጋጅተው እንግዶቻቸውን ይጋብዛሉ፡፡ አውራጅ ዘርግተው እና ጋናቸውን አዘንብለው እንግዶቻቸውን ፆም ያስፈታሉ፡፡ ሳይቀምሱ መሄድ አገር እንደነውር ይቆጠራልና ‹‹አፈር ስሆን›› ብሎ መለመን የተለመደ ባህል ነው፡፡
የክርስቶስ ልደት በታቦር ተራራ እንዲህ ይከበራል፡፡ ቀጣዩ የውሎ ጊዜ የወጣቶች እና የልጃ ገረዶች መድመቂያ ነው፡፡ ታቦቱ ከመንበሩ ካህናቱ ከየአድባሩ ወጥተው በታቦር ተራራ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ይከበራል፡፡
የተክሌ አቋቋም ትምህርት ቤት ተማሪዎች በዝማሬ፣ ወጣቶች በሆታ እና ልጃ ገረዶች በእልልታ ቀኑን በተለየ ሁኔታ ያደምቁታል፡፡ ሌሊቱን በፀሎት እና ጠዋት እንግዶቻቸውን ፆም ለማስፈታት በዝግጅት የሚያሳልፉት እናቶች አሁን ደግሞ ወደቤታቸው ለመሄድ ላልይበላን በታቦር እንዲህ ይለምኑታል ‹‹በል ማረኝ እና ልውረድ ቤቴ
ቅዱስ ላልይበላ የዋሻው አባቴ››
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ፎቶ፡- ትዕግስት ዓለሙ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleንጉሡ ተወልዷል ምድርም በብርሃን ተሞልታለች
Next article‹‹ድርጊቱ የታላቋን አሜሪካ ክብር የማይመጥን አሳፋሪ ተግባር ነው›› የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን