ንጉሡ ተወልዷል ምድርም በብርሃን ተሞልታለች

251
<<ንጉሡ ተወልዷል ምድርም በብርሃን ተሞልታለች>>
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 29/2013 ዓ.ም (አብመድ) አዳም በሲዖል ተጥሏል፣ ትሉ የማያንቀላፋ ፣ እሳቱ የማይጠፋ ሲዖል ለአዳምና ለሔዋን መኖሪያቸው ሆኗል፡፡ በሲዖል የተጣሉ ነብሳት ተስፋ የተደረገላቸውን ቀን ይናፍቃሉ፡፡ አዳም በበደሉ የወጣባት ገነት በእሳታዊ መላዕክ በብርሃን ሰይፍ ትጠበቃለች፣ የተስፋው ዘመን ደርሶ ቃል ሰው ሆኖ፣ የጥፋት ዘመን አልፎ የምኅረት ዘመን እስኪመጣ ድረስ ማንም አይገባባትም። ጊዜ ሳይለካ፣ በማይመረመር ቅድመ ዓለም፣ የማይመረመር አምላክ ይኖር ነበር። በሔዋን የተዘጋውን ገነት የምታስከፍት፣ ለጌታ ማደሪያ የምትሆን እመቤት በምድር ታስፈልግ ነበር። ፍጥረታት ሳይፈጠሩ የሰው ልጅም ሳይበድል፣ ለእናትነት የተመረጠች እመቤት ከሀናና ከእያቄም አብራክ ተገኘች፡፡
የአዳምና የሔዋን ሀጥያት ያልተላለፈባት፣ ገነትና መንግሥተ ሰማያት ተዘጋጅተው የሚጠብቋት፣ መላዕክትና ሰው የሚያመስግኗት፣ ፈጣሪዋ የመረጣት፣ ንጽሒት እመቤት በዚያች ምድር ተወለደች፡፡ ሶስት ዓመት በእናትና አባቷ ቤት፣ 12 ዓመታት ደግሞ በቤተ መቅደስ አደገች፡፡ ምግቧ ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ አልነበረም፣ በሰማይ የመላዕክቱን ዝማሬ፣ በምድርም የካህናቱን ምስጋና፣ ዜማና ዝማሜ እያዳመጠች፣ በልቧ መልካሙን ሁሉ እያሰበች፣ በምግባሯም በሀሳቧም መልካም ብቻ እየሰራች አደገች፡፡ ይህችን የተመረጠች እመቤት በዘመኑ የነበሩ አይሁዳዊያን ቤተመቅደሳችንን ታሳድፋለችና ትውጣ ብለው ከቤተመቅደስ አስወጧት። እርሷ ግን ለጌታዋ ማደሪያ መንበር ትሆን ዘንድ አስቀድማ የተመረጠች ነበረች እንጂ መቅደስ የምታረክስ አልነበረችም። ማርያም ከቤተመቅደስ ስትወጣ በካህኑ ዘካሪያስ ልመና አረጋዊው ዮሴፍ እንዲጠብቃት ተመረጠ።
የመዳን ቀን ደረሰ፣ ትንቢት ሊፈፀም፣ ተስፋ እውን ሊሆን ሲል እግዚአብሔር ከላይ ከአርያም ሆኖ ምድርን ተመለከታት፡፡ በስድስተኛውም ወር መላኩ ገብርኤል በእግዚአብሔር ፊት ፀጋን ወደተቸረችው ድንግል ማርያም ተላከ፡፡ የምስራቹን ሊያበስራት። እውነተኛውን ቃል ለእውነተኛዋ እመቤት፣ እውነተኛው መልአክ ይዞት ወረደ። ለተመረጠችው እመቤት የምስራቹን ነግሯት ተመለሰ። የነቢያት ትንቢታቸው፣ የአዳምና የሔዋን ተስፋቸው እውን ሊሆን ቀርቧል። ንፅሒት እመቤት የሆነች እናቱ ያ ለወንድ ዘር በመንፈስ ቅዱስ ፀነሰች። ፅንሱን ዘር አልቀደመውም። ወራት ተቆጠሩ።
የተስፋው ቀን እየተቃረበ ሄደ። በሲዖል የተጣሉ ነብሳት ከእሳት ወጥተው ሊያርፉ እየተቃረቡ ነው። ሰማይና ምድር ከመፈጠራቸው በፊት የነበረ፣ እነርሱንም የፈጠረ፣ እነርሱም ሲያልፉ የሚኖር አምላክ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወሰነ፡፡ ከሰው ማርያም ከስፍራም ቤተልሔም ተመርጣለችና ቸርና ሩህሩህ የሆነ አምላክ በቤተልሔም ተወለደ። ቤተልሔም ማለት ቤተ ሕብስት የእንጀራ ቤት ማለት ነው ይላሉ ሊቃውንት፣ ቤት ማለት ማርያም ስትሆን ልሔም ደግሞ ለጌታ የተሰጠ ነው ብለው ያሜሰጥሩታል።
<< አንቺ ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ አንቺ በይሁዳ አዕላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ ከአንቺ ዘንድ አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ በእስራኤል ላይ ገዢ የሚሆን ይወጣልኛል>> እንዳለ መፅሐፍ። ኤፍራታ ማለትም ፍሬን የተሸከመች ማለት ነው ይሏታል። << ማርያም ፈጣሪዋን ወለደችው፣ በመጠቅለያም ጠቀለለችው>> እንዳለ ዘማሪው፣ ሰማይ ዙፋኑ ምድርም የእግሩ መረገጫ የሆነ አምላክ በከብቶች በረት ተወለደ። በጨርቅ ተጠቀለለ። እረኞች አዩት፣ መላዕክት አመሰገኑት፣ከሰማይ እስከ ምድር አንዣበቡለት፣ እንስሳት ሙቀት ሰጡት፣ ሠረቀ በምሥራቅ እንዳለ በምሥረቅ ፀሐይ ወጣ፡፡
የጨለማው ዘመን አለፈ። ቁልቁል ሲቆጠር የነበረው ዘመን ሽቅብ ይቆጠር ጀመር። ሰባ ሰገል ሰገዱለት ወርቅ፣ እጣን እና ከርቤ አመጡለት። ወርቁን ለመንግሥቱ፣ እጣኑን ለክህቱ፣ ከርቤውን ለሞቱ፤ ይላሉ አበው። በኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ የጥል ግድግዳ ፈረሰ፣ ሰውና መላዕክት በአንድነት ዘመሩ፣ እግዚአብሔር በሰማይ አራት መንበር አሉት ይላሉ አበው፡፡ ክሩቤል ዙፋኑን ተሸክመውለት ካህናተ ሰማይ ሱራፌል ፊቱን ሳያዩት ስሉስ ቅዱስ እያሉ የሚያመሰግኑት ሆኖ ሳለ በበረት ተወለደ። ሁሉም ያለው ምንም እንደሌለው ተወለደ፣ ፀሐይ እንድታሞቀው፣ ጨረቃ ከጭፍሮቿ ከከዋከብት ጋር እንድታደምቀው ማዘዝ እየቻለ በበረት በተገኙ ከብቶች ትንፋሽ ሞቀ፡፡ ትሁት ነውና ትህትናን አስተማረ። ማርያም ከመፀነሷ አስቀድሞ መልአከ እግዚአብሔር ስሙን ኢየሱስ ትይዋለሽ እንዳላት ኢየሱስ አለችው።
በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ። በሞት ጨለማ ጥላ ስር የሚኖሩ ብርሃን ወጣላቸው። እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ሁሉ ያዘጋጄውን ማዳን ሳያይ እንዳይሞት የተነገረለት አረጋዊው ስምዖን በኢየሩሳሌም ይኖር ነበር። አረጋዊ ስምዖን የእስራኤልን መፅናናት ይጠባበቅ ነበር። ታላቁ ስምዖን የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ ነበር። ስምዖን የእግዚአብሔርን የማዳን ቀን በተስፋ እየተጠባበቀ 500 ዓመታትን ኖረ።
ኢየሱስን ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት። በኢየሩሳሌም የጌታን ማዳን የሚጠባበቀው ስምዖን ተዳክሞ ነበር። መንፈስ ቅዱስ አጠንክሮ ወደ ምኩራብ ወሰደው። ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስን ወደ ቤተመቅደስ ባስገቡት ጊዜ አረጋዊው ስምዖን ተቀብሎ አቀፈው ኃይልና ብርታት ሆነው። ስሞዖንም << ጌታ ሆይ አሁን እንደቃልህ ባርያህን በሠላም ታሰናብታለህ። ዐይኖቼ በሠው ሁሉ ፊት ያዘጋጄኸውን ማዳን አይተዋልና ይህም ለአሕዛብ ሁሉ የሚገለጥ ብርሃን ለሕዝበ እስራኤልም ክብር ነው አለ። እናቱ ማርያምን ግን እንደጦር የሚከፍል ሀዘን በልብሽ ያድራል አላት>> የልጇ የመስቀል ላይ ሞት ልብ የሚከፍል ሀዘን ነውና፣ ክርስቲያኖች ዛሬ በዳዊት ከተማ ታላቅ እርሱ ኢየሱስ ከርስቶስ ተወልዷል፡፡ ‹‹የምሥራች ደስ ይበለን፣ የዓለም መድኃኒት ተወለድልን›› እያሉ ያመሰገኑታል፡፡
‹‹ ከአባቱ ሳይወጣ መጣ፣ ከአኗኗሩ ሳይለይ ወረደ፣ ከሦስትነቱ ሳይለይ መጣ፣ ከአንድነቱም ሳይለይ ወረደ፣ ከዙፋኑም ሳይለይ በስጋ ልጅ አደረ፣ ከመልዓቱ ሳይወሰን በማሕፀን ተፀነሰ፣ በላይ ሳይጎድል በማሕፀን ተወሰነ፣ በታችም ሳይጨመርበት ተወለደ›› እንዳለ ቃል ከሰማይ ወረደ፣ በምድርም ሰው ሆነ፡፡ የፈጠራት ምድርና ከሁሉም ፍጡር አስበልጦ የፈጠራቸው የሰው ልጆች ግን እንኳን ደህና መጣህ አላሉትም፤ ለምን መጣህ ብለው አሰቃዩት እንጂ፡፡ ለምን ቢሉ እውነት የሆነ አምላክ እውነትን ይዞ መጥቷልና፣ ከእውነት ለመሸሽ እውነተኛውን ማሳደድ ነበረባቸው፡፡
በምድር እንደ እውነት የተሰቃዬ የለም። እውነት ተገርፏል፣ ተሰቃይቷል፣ እሬት ጠጥቷል፣ በጦር ተወግቷል፣ ተሰቅሏል፣ ማርያም የአራስነት ጊዜዋ ሳይፈፀም ሄርዶስ አሳደዳት። አሸናፊውን ታቅፋ የማይቻለውን አዝላ ቃል ነውና በበረሃ ተሰደደች። የሕፃኑን ሞት የሚሹ ሞተዋልና ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ ብሎ መላእከ እግዚአብሔር እስኪነግራቸው ድረስ በስደት ቆዩ። የስደት ዘመኗም ሦስት ዓመት ከስድስት ወራት ነበር።
ከስደት እንደተመለሱ በነቢያት <<ናዝራዊው ኢየሱስ>> ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈፀም ዘንድ ናዝሬት በምትባል ከተማ ከልጇ ጋር ኖሩ። ጥቂት በጥቂት አደገ። ሕፃናትን የሚያሳድገው ጌታ እንደ ሕፃን አደገ። ድውያነ ስጋን በታምራት፣ ድውያነ ነብስን በትምህርት ይፈውስ ነበር፡፡ እንደ እግዚአብሔር እየሰራ እንደ ሰው እየተመላለሰ ከሀጥያት በቀር ፍፁም ሰው ሆነ። ለእናቱም እየታዘዘ በጥበብና በሞገስ አደገ። በዋለበት እየዋሉ ባደረበት እያደሩ ከአንደበቱ የሚወጡትን የእውነትና የድኅነት ቃላት ለመስማት የሚጓጉት በዙ፡፡ ገሚሱ ቃሉን ለመስማት፣ ሌላው ደግሞ ከሕብስት ለመካፈል፣ ከፊሉም ከደዌያቸው ለመፈወስ ይከተሉት ነበር፡፡ ለሁሉም እንደሚገባም በምሳሌ እያደረገ፣ ሕይወት የሆነ አምላክ፣ ሕይወት የሆነ ቃል ወንጌልን አስተማረ፡፡ ለአዘኑት መጽናናት፣ ለወደቁት መነሳት፣ ለደከሙት ብርታት፣ ለሞቱት ሕይወት ሆነ፡፡
ጌታ ለምን ተወደለ ? ሲሉ ሊቃውንት ለአዳምና ለሔዋን የገባላቸውን ቃል ኪዳን ለመፈፀም፣ ነቢያት ዘመን እየቆጠሩ ፣ ትንቢት እየነገሩ ይናገሩ ነበርና ትንቢተ ነብያትን ለመፈፀም ተወለደ። ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ ተወለደ። በሰው ልጅ ሀጥያት የረከሰችውን ምድር ሊቀድሳት ተወለደ። የሰው ልጅ እንዳይታበይ እኔ ነኝ ፈጣሪ እንዳይል ያሳዬው ዘንድ ተወለደ ይላሉ። << በኤፍራታ ሰማነው በዱር ውስጥም አገኜነው>> እንዳለ በኤፍራታ ተገኝቷል።
ኢትዮጵያዊያን ሊቃውንት ኢየሱስ በታኅሣሥ 29 ቀን ተወለደ ብለው መፃህፍቱን አቋጥረው ቀኑን አግኝተዋል። በዚህ ቀን ስለ ስሙና ስለ ኃያልነቱ ሊቃውንት ያመሰግኑታል፣ምዕምናን አቤቱ ማኅረን እያሉ ይለምኑታል። << የነቢያት ሀገራቸው ቤተልሔም ሆይ ደስ ይበልሽ ክርስቶስ በአንቺ ተወልዷልና>> እነሆ ንጉሡ ተወልዷል። ምድርም በብርሃን ተሞልታለች። ተስፋም እውን ሆኗል። የመከራው ዘመንም አልፏል።
ክርስቲያኖች የተወለደውን አምላካቸውን የሚያመሰግኑበት የልደቱ ቀን ዛሬ ነው። እንኳን አደረሳችሁ። መልካም በዓል።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article<<በምድር ንጉሥ በሰማይ ቅዱስ>>
Next articleየልደት በዓል በታቦር ተራራ!