<<በምድር ንጉሥ በሰማይ ቅዱስ>>

450
<<በምድር ንጉሥ በሰማይ ቅዱስ>> ቅዱስ ነው ቅድስናን በትጋት ይፈፅማል። ንጉሥ ነው ሀገር ይመራል ያስተዳድራል። ነቅዓ ሀይማኖት ወማኅደረ ጥበብ ይሉታል። ቅድስናን ከንግሥና አጣምሮ የያዘ ቅን አሳቢ፣ በመልካም መንገድ ብቻ ተጓዥ ነው። ምርሐ ተክለሃይማኖት ሞሰበወርቅን አገባ ከሞሰበ ወርቅም ጠጠውድምን፣ ግርማ ስዩምን፣ትርድአነ ገበዝን እና ዛን ስዩምን(ዣን ስዩም) ወለደ። ግርማ ስዩም ይምርሐነ ክርስቶስን ወለደ። ጠጠውድምም ገብረመስቀልን ወለደ። ገብረ መስቀል አቡነ አሮንን ወለደ። ዛን ስዩም ዑጽፍትን አግብቶ ሐርቤን ስመ መንግሥቱ ገበረ ማርያምንና ርብቃን ወለደ። ሐርቤን አረቦች ቀኑዳ ሲሉት ምዕራባውያን ሲኖዳ ወይም ሺኖዳ ይሉታል። ሐርቤ ከመርከዜ አዳም ነአኩቶ ለአብን ወለደ። ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ 40 ዓመታትን ከገዛ በኋላ ተሰውሯል ይባላል። ዛን ስዩም የነ ሐርቤ እናት ስትሞትበት ኬርዎርናን አገባ። ኬርዎርና ማለት በአገውኛ ቋንቋ ቤተክርስቲያን ማለት ነው ይሉታል ሊቃውንት። ዛን ስዩም ኬርዎርናን አግብቶ ሲኖር በመጋቢት 28 ቀን በ1100ዓ.ም የእግዚአብሔር መላዕክ ወደ እርሷ መጥቶ ደስ ይበልሽ ከአንቺ የሚወለደው ልጅ የተመረጠ ነው አላት። ስሙን ላል ይበላ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ስሙ ነአኩቶለአብ፣ ስሙ አሠረ ክርስቶስ ትርጓሜውም የክርስቶስን ፈለግ የሚከተል፣ ስሙ ይምርሐ ይህ ማለት ደግሞ በሥውር ከኤሊያስና ዕዝራ ጋር በገነት የሚኖር ማለት ነው። ለኬርዎርና መላእክ ካበሰራት በኋላ በመጋቢት 29 ቀን 1100 ዓ.ም ፀነሰች። በታኅሣሥ 29 ቀን ወለደችው።የተወለደበትም በደብረ ሮሐ ነው። ፅንሰቱና ውልደቱም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ተመሳሳይ ነው ይላሉ አበው። ሕፃኑ ተወለደ። ነጫጭ ንቦች ከበቡት። ከውስጥ ያለውን ወደውጭ አናስወጣም አሉ ከውጭ ያለውንም ወደ ውስጥ አናስገባም አሉ። ንቦቹ በከንፈሩ አርፈው የእናቱን ወተት ከመጥባቱ አስቀድሞ ማር አቀመሱት። እናቱም ተገረመች። ክርስቶስ ያን ሕፃን የመረጠው እንደ ኤርሚያስ በማህጸን ሳለ ነበር ይላሉ። እናቱም በልጇ ላይ ያዬችውን ታምር በመመልከት ልጇን ላል ይበላ አለች። ንቦች ማርን ተባብረው አቀመሱት አለች። ላል ማለት በአገውኛ ማር ማለት ነው። እናቱም የልጇ ቅዱስነት አስቀድሞ ገብቷት ነበርና ንብ እንኳን ገዢዋን አወቀ አለች ይባላል። ከመወለዱ በፊት የእግዚአብሔር መልዓክ ከእርሷ የሚወለደው ታላቅ የሆነና ስሙም ላል ይበላ ይባላል ብሎ ነግሯት ስለነበር ላል ይበላ አለችውም ይሉታል፡፡ አጤ ካሌብ ባሰሯት በማይ ማርያም በተባለች ደብር ክርስትና ተነሳ፡፡ የክርስትና ስሙን አሰረ ክርስቶስ ተባለ፡፡ የክርስቶስን መንገድ የሚከተል ማለት ነው፡፡ ስድስት ዓመት ሲሞላውም አባ ዳንኤል የተባሉ መምህር ተቀጥረውለት የመንፈሳዊ ትምህርቱን ተከታተለ፡፡ ትምህርቱን እየተከታተለ እያለ በልጅነት እድሜው ወላጆቹን በተከታታይ አጣ፡፡ ልቡ አዘነ። ከተዘጋጀው መንገድና ክብር ግን አልቀረም። ወደ ጎጃምም አቅንቶ ሕገ እግዚአብሔርን ተምሮ ወደ ሮሐ ተመለሰ፡፡ ከጎጃም ከተመለስም በኋላ በታላቅ ወንድሙ ሐርቤ ስመ መንግሥቱ ገብረ ማርያም ቤተመንግሥት ተቀምጦ ስርዓተ መንግሥቱን ይከታተላል ነበር። ላል ይበላ በሰው ዘንድም ተወዳጅ ነበር፡፡ ወደፊትም እንደሚነግሥ ትንቢት ይነገርለት ጀመረ፡፡ ላል ይበላ ይነግሳል ከወንድሙ በትረ መንግሥቱን ይረከባል የሚባለውን ትንቢት ሲነገር የአባቱ ልጅ ታላቅ እህቱ ርብቃ ሰማች፡፡ ቅናት አደረባት፡፡ አንዳንዶች ፍቅረ ንግስትነት ስለ ነበረባትና ከወንድሟ በትረ መንግስቱን መረከብ ትሻ ስለነበር ላል ይበላን አስቀድማ ማጥፋት ፈለገች ይላሉ። አንዳንዶች ደግሞ ላል ይበላ የእናቷ ልጅ ስላልሆነ ለእናቷ ልጅ ለሐርቤ አድልታ ሐርቤ በንግስናው እንዲቆይ ትሻ ስለነበር ላል ይበላን ልታጣፈው አሰበች ይላሉ። በዚያ ዘመን ላል ይበላ ሆዱን ያመው ስለነበር የጌታውን ስቅለት እያስታወሰ አርብ አርብ የኮሶ መድኃኒት ይጠጣ ነበር። እህቱ ርብቃም በዚህ ወቅት ለኮሶ ማርከሻ ብላ መርዝ ሰጠችው። ከላል ይበላ ጋር አንድ ጠባቂ ውሻና አንድ አገልጋይ ዲያቆን አብረውት ይኖሩ ነበር። ላል ይበላ ምንም ከመቅመሱ በፊት ዲያቆኑ ይቀምሰዋል። በዚያን ጊዜም ዲያቆኑ አስቀድሞ ቀመሰውና ሞተ። ውሻውም ዲያቆኑ በጣረሞት ላይ በነበረበት ጊዜ ያፈሰሰውን ቀምሶ ሞተ። ላል ይበላም አዘነ። በእኔ ምክንያት ንፁሓኑ ሞተው እኔም መሞት አለብኝ አለ። መርዙንም አንስቶ ጠጣው። የሞተም መሰለ። ሰው ተሰበሰበ። አስቀድሞ ተመርጧልና ዝም አሉ። << የእግዚአብሔርን አገልጋዮች የሚገድል መድኃኒት ቢጠጡ ሊገድላቸው አይችልም>> እንዳለ መፅሐፍ ሳይሞት ቀረ። በዚያም ጊዜ ነብሱ ሳትወጣ ወደፈጣሪዋ ሄዳ ነበር ይላሉ አበው። << በሕፃናት የመረጥኩህ አሁንም በምክንያት የጠራውህ እኔ ነኝ አንተ ከዛሬ ጀምሮ በምድር የከበርክ ትሆናለህ። ግድግዳዎችም ሆነ ጣሪያቸው ያለ ማገር ያለ ጭቃ በአንድ የማይያዙ በመልካቸው በቁመታቸው፣ በስፋታቸውና በርዝመታቸው የማይመሳሰሉ አብያተ መቅደሶችን ታንፃለህ … ጥበብህን ሰምተው ለሚያዩህ እስከ ዘላለም ሲያደንቁህ ይኖራሉ። በምትሰራበትም ጊዜ የሚያግዙህ መላዕክት እንጂ ሰዎች አይደሉም>> አለው ይላሉ አበው። ላል ይበላ ከወደቀበህ ተነሳ። ከበውት ቆመው የነበሩት ደነገጡ። እርሱም ከእህቴ በላይ ታማኝ ማንን ላገኝ ይቻለኛል በማለት ከሰው ተለይቶ ከአራዊት ጋር ለመኖር ወደ ዱር ገባ። በዚያውም ሲኖር የእግዚአብሔር መላእክ ወደ አለበት መጣ። ወደ አንተ የምትመጣ ሴት አለችና እርሷ የክብር ባለቤትህ ናት እንድትጋቡም ፈጣሪ ፈቅዷልና አለው። የተባለውን ፈፀመ። መስቀለ ክብራንም አገኛት። በፈቀደው መሰረት በፀጋው ተጋቡ። ወደ ኢየሩሳሌምም ሄደ። ክርስቶስ የተመላለሰባቸውን ቦታዎች ተመለከተ። አደነቃቸውም። ቀደም ሲል በሰማይ ቆዬት ሲልም በምድራዊት ኢየሩሳሌም ያያቸውን ሥራዎች የሚሠራበት ጊዜ ደርሶ ነበርና ወደሀገሩ ተመለሰ።መንግሥቱንም ከወንድሙ እንደሚቀበል ተነገረው። ወደ ሮሐ ገሰገሰሰ። ለእርሱ የታዬው ሁሉ አብረው ሳይኖሩም ለሚስቱም ይታያት ነበር። ከወንድሙ ከሐርቤ ስመ መንግሥቱ ገብረ ማርያም ጋር ተገናኙ። ሐርቤ በድሎት ነበርና ይቅርታ ተባባሉ። ይቅርታ ያወረዱበት ስፍራም ሸጎላ ይባላል። ሐርቤና ላል ይበላ የሚቆሙበት ሥፍራ ሶራ ምንጣፍ ተነጥፎለት ነበርና አካባቢው ሶራ እየተባለ ይጠራልም ይባላል። ሐርቤም ንግሥናውን አስረከበ። ስመ መንግሥቱም ገብረ መስቀል ተባለ። ይህም << መዋዔ ፀር ዘኢይትመዋዕ ለፀር>> ጠለትን የሚያሸንፍ ለጠላት የማይሸነፍ ነው ይላሉ ሊቃውንት። በሮሐ ከተማ የሚገኙትን ውብ አብያተክርስቲያናት ከማነፁም አስቀድሞ ከላል ይበላ ከተማ በምሥራቅ ንፍቅ በሚገኝ ተራራ ላይ አሸተን ማርያምን ገንብቷል። ከአሸተን ማርያም ወርዶ በተፈቀደው ቦታ፣ የተፈቀደውን ሥራ ከሌላ የትም ያልተገኙ አብያተክርስቲያናትን ማነፅ ጀመረ። በቤተ ማርያም ጀመረ በቤተ ጊዮርጊስ ፈፀመ። ለእርሱም ቤት አልነበረውም በድንኳን ይኖር ነበር እንጂ። ላል ይበላም በቅድስናና በንግሥና ኢትዮጵያን ለ40 ዓመታት በፍቅር ገዛ። በምድር ንጉሥ ነው በሰማይ ቅዱስ ነው። ምድራዊ ኢየሩሳሌምን በስጋ ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን በመንፈስ አይቷል። ያዬውንም በምድር ገንብቷል። ላል ይበላ ከተቸረውና ከደረሰበት ጥበብ ዓለም አልደረሰችም። የምትደርስም አትመስልም። እንዲያ አይነት ጥበብ ለኢትዮጵያ፣ ለኢትዮጵያዊውና ለኢትዮጵያውያን ብቻ ተሰጠ። ዓለም ይደነቅበታል። እነሆ የቅዱሱና ንጉሡ ልደት ዛሬ ነው። ታላቅ ነህና እንኳን ተወለድክ። ሥራዎችህ ለኢትዮጵያውያን ኩራታችን፣ እንጀራችን፣ ምልክታችን፣ መመኪያችን እና የስልጣኔ ማሳያ አሻራችን ሆነዋናል። እንኳን አደረሳችሁ።
በታርቆ ክንዴ
Previous articleበነጃሺ መስጅድና መካነ ቅርስ ላይ የደረሰውን ጥቃት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አወገዘ፡፡
Next articleንጉሡ ተወልዷል ምድርም በብርሃን ተሞልታለች