በነጃሺ መስጅድና መካነ ቅርስ ላይ የደረሰውን ጥቃት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አወገዘ፡፡

310
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 28/2013ዓ.ም (አብመድ) በትግራይ ክልል በሚገኘው ታላቁ ነጃሺ መስጅድና ታሪካዊ መካነ ቅርስ ላይ የደረሰውን ጥቃት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አወገዘ፡፡
ጠቅላይ ምክር ቤቱ ቅርሱ የደረሰበትን የጉዳት መጠን የሚያጣራ ቡድን ወደ ስፍራው ለመላክ መዘጋጀቱንም ገልጿል።
የጠቅላይ ምክር ቤቱ ጸሃፊ ሼህ ቃሲም መሃመድ ታጁዲን በሰጡት መግለጫ “ነጃሺ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ቅርስ ነው” ብለዋል።
ነጃሺ በዓለም የመጀመሪያው የስደተኞች መብትና ሰዎች የፈለጉትን እምነት በነጻነት እንዲያራምዱ በንጉስ ነጃሺ የተፈቀደበት ታሪካዊ ቦታ መሆኑንም አብራርተዋል።
ቦታው የታላቁ ንጉሥ ነጃሺ እና ሌሎች የነብዩ ሙሃመድ ባልደረቦች መካነ መቃብር ስፍራና በዓለም ከሚገኙ ጥቂት ጥንታዊ መስጅዶች አንዱና ታሪካዊ ስፍራ መሆኑንም ተናግረዋል። በመሆኑም በታላቁ ነጃሺ መስጅድና የመካነ መቃብር ቅርስ ላይ በደረሰው ጥቃት ጠቅላይ ምክር ቤቱ ማዘኑን ገልጸዋል።
በመስጅዱና ቅርሱ ላይ የተፈፀመው ጥቃት ኢትዮጵያዊያንን ብቻ ሳይሆን የዓለም ሙስሊሞችንም ያሳዘነ ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል።
የሶሪያን ስደተኞች ጀርመን ስትቀበል መራሂተ መንግስት አንጌላ መርክል “እንደ ኢትዮጵያ ንጉስ ነጃሺ ስደተኞችን በተቸገሩና መሄጃ ባጡ ጊዜ እንዳስጠለለው እኛም ተቀብለን እናስተናግዳለን’’ ማለታቸውን ሼህ ቃሲም በመግለጫው በማስታወስ የንጉስ ነጃሺን ታላቅነት አንስተዋል።
ምክር ቤቱ በመስጅዱና ታሪካዊ መካነ ቅርሱ ላይ የደረሰውን ጉዳት ትክክለኛ መረጃ እና ማብራሪያ እንዲሰጠው ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ምክር ቤቱ ቅርሱ የደረሰበትን የጉዳት መጠን የሚያጣራ ቡድን ወደ ስፍራው በመላክ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡
ለመስጅዱ ጥገና ለማድረግ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
መንግሥት ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ለታሪካዊ ቦታዎች እና ቅርሶች ተገቢውን ትኩረትና ልዩ ጥበቃ እንዲያደርግም ምክር ቤቱ ማሳሰቡን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleምዕመኑ የልደት በዓልን ሲያከብር የተፈናቀሉ እና ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በማሰብ እና በመርዳት ሊሆን እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ገለፁ፡፡
Next article<<በምድር ንጉሥ በሰማይ ቅዱስ>>