ምዕመኑ የልደት በዓልን ሲያከብር የተፈናቀሉ እና ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በማሰብ እና በመርዳት ሊሆን እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ገለፁ፡፡

105
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 28/2013 ዓ.ም (አብመድ) በጎንደር የሃይማኖት አባቶች የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የማዕከላዊ እና ምዕራብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዮሐንስ እና የጎንደር ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት ሕብረት ሰብሳቢ መጋቢ ሞላ እምሩ ናቸው የእንኳን መልዕክት ያስተላለፉት፡፡
የሀይማኖት አባቶቹ እንዳሉት ሠላም በምድር እንዲሰፍን የክርስቶስን አርዓያነት መከተል ይገባል፤ ሁሉም ከራሱ አልፎ ለሌላው ማሰብ፣ መርዳትና መተዛዘን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የልደት በዓልን ምዕመኑ ሲያከብር ሁሉም በያለበት የተፈናቀሉ እና ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በማሰብ እና በመርዳት ካለው በማካፈል ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ክርስቶስ ዝቅ ማለትን ለሰው ልጆች እንዳስተማረ እና አርዓያነቱን እንዲከተሉ እንዳዘዘ ምዕመኑ ተረድቶ በቋንቋ፣ በጎሳ እና በድንበር ከመለያየት ወጥቶ ከራስ ይልቅ ሰዎችን ማስቀደም እንደሚገባው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በዓሉ በሠላም እንዲጠናቀቅ ኅብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን መሥራት እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ምስጋናው ብርሃኔ- ከጎንደር
Previous articleበቅድስቲቷ ከተማ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አየኋቸው
Next articleበነጃሺ መስጅድና መካነ ቅርስ ላይ የደረሰውን ጥቃት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አወገዘ፡፡