በቅድስቲቷ ከተማ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አየኋቸው

275

ኢትዮጵያዊነት ለትህትና ዝቅ ብሎ ለክብር ከፍ ማለት ነው። ኢትዮጵያዊነት ታግሶ ማሸነፍ፣ ኢትዮጵያዊነት አስተውሎ ማለፍ፣ ኢትዮጵያዊነት ትህትና ፣ ኢትዮጵያዊነት ምስጋና፣ ኢትዮጵያዊነት መልካም ስብዕና፣ ኢትዮጵያዊነት ከፍ ያለ ልዕልና ነው። ኢትዮጵያዊነት እውነት፣ ኢትዮጵያዊነት እምነት፣ ኢትዮጵያዊነት ውበት፣ ኢትዮጵያዊነት መልካምነት ነው።

ኢትዮጵያዊያን ለፍቅር ዝቅ ይላሉ፣ ለትህትና እጅ ይነሳሉ፣ ለፀሎት ይንበረከካሉ፣ ኢትዮጵያዊያን ክፉ አድራጊን ይመክራሉ፣ መልካም አድራጊን ያመሰግናሉ፣ ጥበብን ያስተምራሉ፣ በጥበብ ይሠራሉ፣ በሚስጥር ይኖራሉ። በሀገራቸውና በክብራቸው ለሚመጣ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በጋራ ዘምተው፣ በጋራ አሸንፈው ይመለሳሉ፣ ኢትዮጵያዊነት ሕብረት፣ ኢትዮጵያዊነት አሸናፊነት፣ ኢትዮጵያዊነት ተፈላጊነት፣ ኢትዮጵያዊነት ቀደምትነት፣ ኢትዮጵያዊነት የበላይነት ነው። በኢትዮጵያዊነት ልክ ስትሆን ትከበራለህ፣ ትደሰታለህ ትወደዳለህ። ከኢትዮጵያዊነት ልክ ስትወርድ ትዋረዳለህ፣ ኢትዮጵያዊነት መከበሪያ፣ ኢትዮጵያዊነት መታፈሪያ፣ ኢትዮጵያዊነት መኖሪያ ኢትዮጵያዊነት መሻገሪያ ነው።

እግሬ ከመልካሙ ሥፍራ አደረሰኝ። ደስም አለኝ። የእየሱስ ክርስቶስ እና የቅዱስ ላልይበላን የልደት በዓል የሚያከብሩ ምዕምናን በየአቅጣጫው ይገባሉ። በተራራዎች ግርጌ የተሸጎጠችው ቅድሲቲቷ ከተማ እንግዶቿን እየተቀበለች ሽርጉድ ትላለች። መልካሙ የሀገርኛ ለዛ ንግግራቸው ልብን በፍቅር ያርዳል። ምን አይነት መታደል ነው ከዓመት እስከ ዓመት እንግዳ እየተቀበሉ አለመሰልቸት፣ ምን አይነት መመረጥስ ነው ተንከባክቦ መሸኘት፣ በፍቅር ማቆዬት- ስለ እውነት ኢትዮጵያዊነት በዚያች ምድር አለች። አስቀድማ የተመረጠች፣ ዛሬ ያስደመመች፣ ነገም ለማስደመም የተዘጋጄች መልካም ምድር ናት ላል ይበላ። የራስን ጊዜ ሰጥቶ፣ ራስን ለግልጋሎት አዘጋጅቶ በትጋት መኖር ምንኛ መታደል ነው።

መልካሟን ኢትዮጵያ አይቻታለሁ፣ ሰላየኋት ተደስቻለሁ፣ ላሳየኝም ምስጋናም አቅርቢያለሁ። ስቆ መቀበል፣ ተቀብሎ በፍቅር ማቀማጠል፣ አስመችቶ ማሰንበት፣ በትዝታ አስሮ መሸኜት ይችሉበታል። ፍቅራቸው፣ መልካምነታቸው፣ ትጋታቸውና አለመሰልቸታቸው መቼውንም አይረሳም፣ የልደትን በዓል ለማክበር ምዕምናን ወደ ሥፍራው ይጎርፋሉ።

የከተማዋ ነዋሪዎችና ወጣቶች ደግሞ ለአገልግሎት ይፋጠናሉ። የላል ይበላ ነዋሪዎች ታድለዋል፣ ፍቅርና አክብሮት መገለጫቸው ነው። በዚያች ከተማ ድንቅ ነገር አየሁ፡፡ ወጣቶች ወደ አስደናቂዎቹ የላል ይበላ አብያተክርስቲያናት የሚገቡ ሰዎችን ከጠዋት እስከ ማታ ድረስ እግራቸውን ያጥባሉ። ወንድ ሴት፣ ታናሽ ታላቅ፣ ሀብታም ደሃ የለም። ወደ ቤተክርስቲያኑ የሚገባ ሁሉ እኩል ይከበራል። ዝቅ ብለው እግር ያጥባሉ፣ ጎንበስ ብለው ጉልበት ይስማሉ፣ ከላይ በረከት ይወስዳሉ። ገሚሶች የተራበውን ያጎርሳሉ። ድንገት በጉዞ ምክንያት የታመመ ካለም ወደ ሀኪም ቤት ያደርሳሉ። እግር እያጠቡ፣ የተራበን እየመገቡ ለአገልግሎት የሚፋጠኑ ወጣቶች ስለ መልካምነታቸው ሲጠየቁ ዝቅ ብለን ከፍ አልን፣ መልካሙን አድርገን ረካን እንጂ ያጣነው ነገር የለም ነው የሚሉት።

ዘንድሮ ከታኅሣሥ 22 ቀን ጀምረው እግር በማጠብና በማስተናገድ ለአገልግሎት እየተፋጠኑ እንደሆነም ነግረውናል። የተደራጄው መልካም ሥራቸው ከአስርት ዓመታት በላይ የተሻገረ መሆኑንም ነግረውናል።

የላል ይበላ ወጣት የአባቶቹን መልካም ታሪክ በመንገርና በመተግበር ይተጋሉ። ዝቅ ብሎ እግር ማጠብና በረከት መቀበል ኩራታቸው ነው። ቅድስቲቷን ከተማ የረገጡት ሁሉ በመልካም ወጣቶች በሚደረግላቸው ሁሉ ይገረማሉ። ከልብ ይመርቋቸዋል። መልካም ምኞታቸውንም ይገልፁላቸዋል።

ዘንድሮ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ብዙ የውጭ ሀገር ዜጎች ባይመጡም ከአሁን በፊት የወጣቶች መልካምነት የሚደንቃቸው የውጭ ሀገር ዜጎች እንጀራ እየገዙ ለምዕምናን ይሰጥ ዘንድ ያበረክቱላቸው እንደነበርም ወጣቶች ነግረውናል። ዘንድሮ በሥፍራው የመገኘቱ እድል ሳያገኙ ቢቀሩም ብር ልከው እንጀራ እንዲገዛ አድርገዋል ነው ያሉን።

ወጣቶች በሚሰሩት መልካም ሥራ በህሊና ረክተውበታል፣ በመንፈስ ጎልብተውበታል፣ በፀጋ ከብረውበታል፣ ሥፈራውን የረገጠውን ሁሉ አስደምመውታል። መልካም የሆነውን ኢትዮጵያዊ ውብ እሴት ለዓለም ሽጠውታል። ለዚያም ነው የውጭ ሀገር ዜጎች የመልካም ዓላማቸው አጋዥ የሆኑት።

ላል ይበላ የኢትዮጵያ ጌጥ፣ የምድር መልካሙ ስጦታ፣ የሰው ልጅ ደስታ ነው። ኢትዮጵያን ፈልጓት አስደንቃ ታገኟታላችሁ፣ ጉያዋን ዳሱት ትረኩባታላችሁ፣ በኢትዮጵያ የማያረጅ ውበት፣ የማይነጥፍ ደግነት፣ የማይረታ ጀግንነት አለ። በቅድስቲቷ ከተማ አስደናቂ ነገር አለ። ያልተፈታ ሚስጥር፣ ያልተመረመረ እውነት፣ ያማረ ኢትዮጵያዊነት። እኔ መልካምን አይቻለሁ። ኢትዮጵያዊ በመሆኔም አመስግኜ ኮርቻለሁ እናንተስ?

ትሁት መሆን ዋጋው ብዙ ነው። በሚስጥራዊት ሀገር ሚስጥራዊ ባሕል፣ ታሪክ፣ ሀይማኖት፣ ቋንቋና እሴት አለ። ኢትዮጵያውያን በተመረጠች ሀገር የተፈጠርን ሁሉም የተሰጠን፣ ሁሉንም ለሁሉም የሰጠን ድንቅ ሕዝቦች ነን። ድንቅነታችን ያስከብርልናል። ያስወድደናል። እንኳን አደረሳችሁ።

በታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“የተፃፈበትን የብር ኖት አትቀበሉ እየተባለ የሚናፈሰው ወሬ መሠረተ ቢስ ነው” የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
Next articleምዕመኑ የልደት በዓልን ሲያከብር የተፈናቀሉ እና ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በማሰብ እና በመርዳት ሊሆን እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ገለፁ፡፡