በበዓል ገበያ ከምግብ ዘይት በስተቀር የጎላ የዋጋ ጭምሪ እንደሌለ ሸማቾች ተናገሩ፡፡

549

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 28/2013 ዓ.ም (አብመድ) ሀብታም ሽፈራው ትባላለች፤ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ናት፤ በዓልን መሰረት አድርጋ ግብይት ስትፈፅም ነው የገኘናት፤ ሀብታም እንደነገረችን ለበዓል የሚያስፈልጉ እንደ ዶሮ፣ እንቁላል፣ ቅቤ፣ ዘይትና መሰል ሸቀጦች አቅርቦቱ ጥሩ ነው፤ በአብዛኞቹ ላይ ከወትሮው የተለየ የዋጋ ጭማሪም የለም፤ ሰውም በተረጋጋ ሁኔታ እየገዛ ነው፤ ነገር ግን ዘይት ከታሰበው ዋጋ በላይ ጨምሯል ብላለች፡፡

ሌላዋ ሸማች ቆንጅት ሃይሌ በዓልን ተከትሎ ብዙም የዋጋ ጭማሪ እንደሌለ ነገር ግን የዘይት ዋጋ መጨመሩን ነግራናለች፡፡ በዘይት ላይ የተደረገውን የዋጋ ጭማሪ የሚመለከተው አካል ሊፈትሸው ይገባል ብላለች፡፡

ወይዘሮ ዘውዴ ደስታየሁ ማርና ቅቤ ነጋዴ ናቸው፤ የልደት በዓል ገበያ እንደጠበቁት እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በርካታ ሰው በዓልን ተከትሎ ቅቤ፣ ሽንኩርት፣ ዘይት፣ ቲማቲም እና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦችን እየገዛ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ በዓልን ተከትሎ የተጨመረ ዋጋ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፈጠረው ተጽዕኖ ግን ገበያ መቀዛቀዙን ነግረውናል፡፡

እንደ ወይዘሮ ዘውዴ አስተያየት ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት በርካታ እንግዶች ወደ
ባሕር ዳር ይመጡ ነበር፤ እናም ማር እና ቅቤ በደንብ ይሸጥ ነበር፡፡ “ከአርሶ አደሩ የተረከብነውን ምርት በወቅቱ ካልሸጥን ግብርም ሆነ የቤት ኪራይ ለመክፈል እንቸገራለን፡፡ ይህ ጉዳይ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይም ተጽዕኖ ይፈጥራል” ብለዋል፡፡

ምርት ወደ ገበያ በብዛት የሚቀርብበት ወቅት በመሆኑ ከአርሶ አደሩ እየተረከቡ ለተጠቃሚው በተመጣጠነ ዋጋ እያቀረቡ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡ ቅቤ እና ማር አምና በዚህ ወቅት ከነበረው ዋጋ ጋር ሲነፃፀር በዚህ ዓመት ቅናሽ ያለው መሆኑንም ወይዘሮ ዘውዴ ተናግረዋል፡፡

ሸቀጣሸቀጥ ንግድ ላይ ያገኘናቸው አቶ ባንቴ አንተነህ ዘይት ላይ የታየውን የዋጋ ጭማሪ አስመልክቶ “የአቅርቦት ችግር የለም ነገር ግን መንግሥት በእያንዳንዱ የዘይት ጀሪካን ላይ የ6 ብር ከ20 ሳንቲም ጭማሪ በማድረጉ ብቻ አከፋፋዮች ዋጋ ጨምረዋል” ብለዋል፡፡

ሸማቹ በዓልን ብቻ ተከትሎ ለመግዛት የሚያደርገውን ሩጫ ቢቀንስ፤ ጭማሪ መኖሩን ሲሰማ ለምን ብሎ በመጠየቅ መፍትሄ ማምጣት ቢችል፤ መንግሥትም ነገሮችን በጥልቀት በማየት ክፍተቱን ቢሞላ መልካም እንደሚሆን አቶ ባንቴ ጠቅሰዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የሸማች ማኅበራትን በማጠናከር የተረጋጋ አቅርቦት እንዲኖር እየሠራ መሆኑን ገልጿል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የግብይት ቡድን መሪ አቶ ማሞ ተሰማ በመሰረታዊ ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ የአቅርቦት ችግር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰትም በየሳምንቱ ከሰበሰቡት የገበያ ዋጋ ጋር በማወዳደር ጭማሪ አለማሳየቱን እንዳረጋገጡ ነው የጠቀሱት፡፡ የአቅርቦት ችግር እንዳይፈጠርም ሸማች ማኅበራትን በማደራጀት መሰረታዊ ምርቶች ለተጠቃሚ የሚደርሱበትን ሁኔታ መመቻቸቱን ነግረውናል፡፡ በዚህ ሳምንት ዘይት እና በርበሬ ዋጋ ላይ ጭማሪ መታየቱን አቶ ማሞ ገልፀዋል፡፡

መንግሥት ዘይትን ከቀረጥ ነጻ በድጎማ ከሚያስገባቸው ምርቶች ውስጥ አንዱ ነው፤ ነገር ግን ከወደብ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ዘይትን ጨምሮ ያልገቡ ምርቶች በመኖራቸው የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል፡፡ ነገር ግን ከተቀመጠው የዋጋ ዝርዝር አልፎ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ሲከሰት ጥቆማ በማድረግ የእርምት ርምጃ እንደሚወሰድ አቶ ማሞ አመላክተዋል፡፡

ሸማች ማኅበራትን በማጠናከር የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብድር እንዲመቻች መደረጉንም ነግረውናል፡፡ በዚህም የምርት አቅርቦቱ ላይ ችግር አልገጠመንም ነው ያሉት ፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህመት ለልደት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
Next article“የተፃፈበትን የብር ኖት አትቀበሉ እየተባለ የሚናፈሰው ወሬ መሠረተ ቢስ ነው” የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ