በባሕር ዳር ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የምግብ ድጋፍ ተደረገ።

99
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 28/2013 ዓ.ም (አብመድ) ድጋፉን ያደረገው የአማራ ክልል የአደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ነው፡፡
ኮሚሽኑ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ ነው ድጋፍ ያደረገው፡፡
ድጋፍ ከተደረገላቸው ወገኖች መካከል ወይዘሮ ዳሳሽ አበጀ ድጋፉን ባያገኙ ኖሮ በዓሉን ማሳለፍ እንደሚከብዳቸው ተናግረዋል፡፡ “አሁን እንደማንኛውም ሰው ተደስቼ በዓሉን ማሳለፍ እችላለሁ፤ ድጋፍ ላደረጉልኝ አመሠግናለሁ፤ ሀገር ሠላም ቢሆን ነው ድጋፉም የተገኘውና ሀገራችንን ፈጣሪ ይጠብቃት” ብለዋል፡፡
ድጋፍ ከተደረገላቸው ውስጥ ወይዘሮ ዘምዘም መሃመድ አንዷ ናቸው፡፡ መንግሥት ለአቅመ ደካሞችና ለአካል ጉዳተኞች ድጋፍ ማድረጉ ያስመሠግነዋል ብለዋል፡፡ “ሙስሊምም ሆንን ክርስቲያን አንድ ነን ችግር ሲያጋጥመን መረዳዳትም ባሕላችን ነው፡፡ እኛ በእምነታችን ነው እንጂ የምንለያየው ተደጋግፈን በዓላትን አብረን በማሳለፍ የሚለየን የለም” ብለዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶክተር) ማስተባባሪ ኮሚሽኑ በከተማዋ ውስጥ በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የከተማዋን ነዋሪዎች አስቦ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ አበበ (ዶክተር) እንደተናገሩት በዓላት ሲመጡ እና በማንኛዉም ጊዜ ቢሆን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ማሰብና መደገፍ ባሕላችን ብቻ ሳይሆን የሃይማኖቶች አስተምህሮ ግዴታ ነው፡፡
የክልሉ መንግስትም የሕዝቡን ባህልና እሴት ለመጠበቅ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖችን ለመደገፍ በማሰብ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች ከ250 ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለው እንደሚገኙ ያስታወሱት ዶክተር ሙሉነሽ እነዚህን ወገኖች ለመርዳት የመንግሥት ድጋፍ ውስን በመሆኑ ቋሚ መፍትሄ እስኪመጣ ድረስ ማኅበረሰቡ ባዳበረው የመረዳዳት ባሕል መሠረት ድጋፉን ሳያቋርጥ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ የተደረገዉ ድጋፍ በቂ ነው ማለት ሳይሆን የአብሮነት ማሳያ መሆኑን ለመጠቆም ነው ብለዋል፡፡ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ሳይለያይ የመደጋገፍ፣ የመከባበር እና የአንድነት ባሕሉን ማጎልበት ይጠበቅበታል ነው ያሉት አፈ ጉባዔዋ፡፡ ዛሬ የማይከበር ትውልድ ነገ ሌላ ትውልድን አያከብርምና ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል የአብሮነት እሴቱን ማጠናከር ይገባዋል ነው ያሉት፡፡
ድጋፉ የተደረገው ለ1ሺህ አቅመ ደካሞች ነው፤ ለእያንዳንዳቸውም 25 ኪሎግራም የስንዴ ዱቄትና ሦስት ሊትር ዘይት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ሱዳን በሰሜን ዳግላሽ አካባቢ ድንበር ጥሳ ወደ ኢትዮጵያ መግባቷ የሁለቱን ሀገራት የቀደመ ስምምነት የጣሰ ነው” አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ
Next articleበበጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት የሚሰማሩ ወጣቶች ለስልጠና ወደ ዩኒቨርሲቲዎች እየገቡ መሆኑን የሠላም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡