
“ሱዳን በሰሜን ዳግላሽ አካባቢ ድንበር ጥሳ ወደ ኢትዮጵያ መግባቷ የሁለቱን ሀገራት የቀደመ ስምምነት የጣሰ ነው” አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 28/2013 ዓ.ም (አብመድ) ሱዳን በሰሜን ዳግላሽ አካባቢ ድንበር ጥሳ ወደ ኢትዮጵያ መግባቷ የሁለቱን ሀገራት የቀደመ ስምምነት የጣሰ እንደሆነ የሁለቱ ሀገራት የጋራ ድንበር ኮሚሽን አባል አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ ተናገሩ።
የድንበር ችግሩ የሚፈታው በሀገራቱ ስምምነት እና በዓለም አቀፍ መርህ እንደሆነ የጠቀሱት አምባሳደሩ፣ በቅርቡ በድንበር አካባቢ የተፈጠረው ችግር እ.ኤ.አ በ1972 የሰሜን ዳግላሽ አካባቢ ባለበት ነባራዊ ሁኔታ እንዲቆይ የተደረሰውን ስምምነት የጣሰ ነው ብለዋል።
በ1972ቱ የማስታወሻ ልውውጥ መሠረት ድንበሩን ለማካለል የሁለቱ መንግሥታት ከመፍትሔ ሐሳቦች ላይ ሲደርሱ ብቻ ነው ይላል። ይህ ማለት በአካባቢው ያለው ነባራዊ ሁኔታ በሁለቱም ሀገሮች ተከብሮ እንዲቆይ ያስገድዳል ብለዋል።
በቅርቡ ኢትዮጵያ በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ሕግ የማስከበር ሥራ ላይ እንዳለች የሱዳን ጦር በዳግላሽ ሰሜን አካባቢ ድንበር ጥሶ በመግባት ነባራዊ ሁኔታውን አደጋ ላይ መጣሉን አምባሳደር ኢብራሂም ጠቅሰዋል።
የሱዳን ወታደራዊ ኃይሎች ከባድ መሣሪያዎችን በመጠቀም የተደራጁ ጥቃቶችን እንደፈጸሙም አምባሳደሩ አስታውሰዋል።
የአርሶ አደሮችን የግብርና ምርቶችንና መገልገያ መሣሪያዎችንም እንዳወደሙ ጠቅሰዋል። በጥቃቱ ውስጥ ዘረፋ እንደተፈጸመ፣ በርካታ ዜጎችም እንደቆሰሉ፣ እንደተፈናቀሉ እና እንደተገደሉ አምባሳደር ኢብራሂም በመግለጫቸው አንሥተዋል።
የሱዳን ሠራዊት በኃይል ቦታውን ለመያዝ የወሰደው ርምጃ ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር የሚጣረስ ነው ብለዋል።
ሱዳንም እ.አ.አ በ1972 የተደረሰውን ስምምነት በመጣሷ ሊያስጠይቃት እንደሚችልም በመግለጫው ተጠቁሟል።
ስምምነቶችን ተከትሎ በሚደረጉ ንግግሮች ችግሩን መፍታት እና መልካም ጉርብትናን ማስቀጠል የኢትዮጵያ ፍላጎት ነው ተብሏል።
ግጭት ሁለቱንም ሀገራት አትራፊ እንደማያደርግ እና በተቃራኒው ግን የሀገሮችን ዝቅታ ለሚፈልጉ ሦስተኛ ወገኖች መጠቀሚያ እድል እንደሚፈጥር በመረዳት በሰከነ መንገድ ለችግሩ መፍትሔ ማስቀመጥ ይገባል ነው የተባለው።
የኢትዮጵያ እና ሱዳን መንግሥት እንዲሁም የሀገራቱ ሕዝቦች ከዘላቂ ጥቅማቸው እና ግንኙነታቸው በታች የሆነው የድንበር ችግር የፀብ ምንጭ ሊሆን አይገባም፤ ንግግርን ያስቀደመ መፍትሔ ሊቀድም ይገባል መባሉን ኢብኮ ዘግቧል፡፡