የልደት በዓልን በሃሴት፤ኮሮናን በጥንቃቄ እናሳልፍ!

173
የልደት በዓልን በሃሴት፤ኮሮናን በጥንቃቄ እናሳልፍ!
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 28/2013 ዓ.ም (አብመድ) ዛሬም የኮሮናቫይረስ ብዙ ሰዎችን ለልደት በዓል ሳይደርሱ ህይወታቸውን አሳጥቷል፡፡ አሁንም በኮሮናቫይረስ ላለመያዝ ጥንቃቄ ማድረግ የግድ ሆኗል፡፡ በኮሮና ምክንያት በዓለም ላይ ከ1 ሚሊዮን 8 መቶ ሺህ በላይ ሰዎች በሞት ተለይተዋል፡፡
የዘንድሮውን በዓል ለማክበር የታደለ ለቀጣይ ዓመት እንዲደርስ ከፈጣሪ በታች ራሱን ከኮሮና ቫይረስ መጠበቅ እንደሚገባው አሁንም የጤና ባለሙያዎች የጥንቃቄ መልዕክታቸውን እያስተላለፉ ነው፡፡
የዘንድሮው የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ሲከበር ራስን ከኮሮናቫይረስ በመከላከል ሊሆን ይገባል ብለውናል ስለ ጥንቃቄዎቹ መልዕክታቸውን የነገሩን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የቅድመ ማስጠንቀቅ ባለሙያ አቶ አሞኘ በላይ፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስርጭቱ እየጨመረ፤ በፅኑ የሚታመሙና ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ይገኛል፡፡ ታድያ ብልህ ሰው ከሰው ይማራል ነውና ከመዘናጋት ይልቅ አሁንም የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚረዱ የጥንቃቄ መንገዶችን ሳይሰለቹ መተግበር ይገባል ብለዋል አቶ አሞኘ፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች የልደት በዓል ሲከበር በሬ ታርዶ ቅርጫ እየተከፋፈሉ ሰብሰብ ተብሎ ይከበራል፡፡ ጥሬ ስጋን መብላት የሚወዱም በዚህ በዓል ከቅርጫው እያነሱ መብላታቸው አይቀርም፡፡ ታድያ በዓልን ተሰባስቦ ማክበር ጥሩ ቢሆንም የሚያስከትለውን ጉዳት ማሰብና ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ይላሉ የቅድመ ማስጠንቀቅ ባለሙያው፡፡
በተለይ ተሰባስቦ ማክበር፣ ጥሬ ስጋን መመገብና ሌሎች ለቫይረሱ የሚያጋልጡ ልማዶችን ማስቀረት ያስፈልጋል ያሉት አቶ አሞኘ ስጋን በሚገባ አብስሎ መመገብ፣ ርቀትን መጠበቅ፣ እጅን በሳሙና በተደጋጋሚ በመታጠብ (የንፅህና መጠበቂያዎችን መጠቀም) ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምበል በማድረግ ራስንና ወገንን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መጠበቅ ሳይሰለች ሊተገበር ይገባል ብለዋል፡፡
በዓል ሲመጣ ወደ ገበያ ወጥቶ የበዓል መዋያ ግብይቱንና ግርግሩም ይጨምራልና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ሳያደርጉ ወደ ገብያ መውጣት ራስን እና ቤተሰብን ለኮሮና ቫይረስ ስለሚያጋልጥ ያለ ጭምብል ገበያ አይውጡ፤ ከገበያ ሲመለሱም እጅዎን በሳሙና በደንብ ይታጠቡ ነው ያሉት፡፡
በዓል ነውና እንደ ባህልና ልማዳችን እየተጨባበጥን እንኳን አደረሰን መባባልም ለዘንድሮው የገና በዓል አያስፈልግም፤ ወዳጅዎን እና ዘመድዎን ከወደዱ አይጨባበጡ፤ ርቀትዎን ጠብቀው እንኳን አደረሰህ/ሽ ይባባሉ የሚል መልዕክት ከአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለሙያው የተላለፈ መልዕክት ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ሸምስያ በሪሁን
ፎቶ፡- ከድረ ገጽ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ፤ በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ፡፡
Next article“ሱዳን በሰሜን ዳግላሽ አካባቢ ድንበር ጥሳ ወደ ኢትዮጵያ መግባቷ የሁለቱን ሀገራት የቀደመ ስምምነት የጣሰ ነው” አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ