
የወባ በሽታን እ.ኤ.አ በ2030 ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ብሔራዊ ወባን የማጥፋት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ እንቅስቀሴ እየተደረገ መሆኑን ተገለፀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 27/2013 ዓ.ም (አብመድ) በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የወባ በሽታን በመከላከልና በመቆጣጠር ዙሪያ በተከናወነው ተግባር ውጤቶች መመዝገባቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሽታውን ለማጥፋት የሚደረገዉ እንቅስቃሴ አካል በመሆኗ የወባ በሽታን እ.ኤ.አ በ2030 ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ብሔራዊ ወባን የማጥፋት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ በስድስት ክልሎች፣ 12 ዞኖችና 239 ወረዳዎች ወደ ስራ መግባትቱን ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ በተለይ ከኮረናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ጋር ተያይዞ በተፈጠሩና በሌሎችም አንዳንድ ችግሮች ምክንያት የወባ ማጥፋት መለኪያዎች አፈጻጸም ውጤት በሚጠበቀው ደረጃ እየተተገበረ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከወባ ማስወገድ ጋር በተያያዘ የሚታዩ ጠንካራ ጎኖች እንዲሁም ችግሮች ላይ በመመስረት በቀጣይ ስድስት ወራት ትኩረት ተሰጥተው መከናወን ባለባቸው ተግባራት ላይ የስራ መመሪያ ተሰጥቷል ብለዋል፡፡
የወባ ማስወገድ የአፈፃፀም ግምገማ በአዳማ ከተማ ከስደስት ክልሎች አማራ፣ ኦሮምያ፣ ደቡብ፣ ሲዳማ፣ ሐረሪ፣ ከጤና ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማትና ከመድኃኒትና ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ፣ ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከአሐሪ፣ ከልማት አጋር ድርጅቶች፣ ከፌደራል ጤና ሚኒስቴር የወባ ማስወገድ ቡድን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት መካሄዱን የጤና ሚኒስቴር በማኀበራዊ ድረ ገጹ አስታውቋል ፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
