
ከ3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በጎንደር ከተማ ኢንቨስት ለማድረግ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 27/2013 ዓ.ም (አብመድ) በጎንደር ከተማ ከ3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ጥያቄ ማቅረባቸውን ከተማ አስተዳደሩ ገልጿል፡፡
የከተማዋ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ባዩ አቡሃይ ከፍተኛ የቱሪስት ፍስት ያላት የጎንደር ከተማ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተጠቃሚ አልነበረችም፡፡
በተለይም በአካባቢው ከዓመታት በፊት የነበረው አለመረጋጋት በኢንቨስትመንት ፍሰቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡
ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የከተማ አስተዳደሩ ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ ችግሩን ለመፍታት በሰራው ሥራ ሠላም በመረጋገጡ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ባለሀብቶችን ለመሳብና የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማሳደግ ሠላሙን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የአካባቢውን እምቅ ሀብት በማስተዋወቅ በኩል ከፍተኛ ሥራ መሥራቱን ገልፀዋል፡፡
በአካባቢው ለኢንዱስትሪ ጥሬ እቃ የሚሆን ግብዓት መገኘቱና በቂ የሰለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት መኖሩ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ባለሀብቶች በአካባቢው በተለያዩ የልማት መስኮች ለመሰማራት ያሳዩት ተነሳሽነት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ 33 ኢንዱስትሪዎች ማምረት መጀመራቸውንና 60 ኢንዱስትሪዎች ደግሞ ግንባታቸውን በማጠናቀቅ ማሽነሪ በማስገባት ሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በከተማዋ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት ከ3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 75 ባለሀብቶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ለመሰማራት ጥያቄ ማቅረባቸውንም ተናግረዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ጎንደርን የኢንዱስትሪ መዳረሻ ለማድረግ የበለጠ እንደሚሠራ የተናገሩት አቶ ባዩ በተለይም በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት፣ በማኑፋክቸሪንግና ሌሎች ዘርፎች መሠማራት የሚሹ አካላትን ለማስተናገድ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡
“ለዚህ ስኬቱ ከተማ አስተዳደሩ ከፌዴራልና ከክልሉ መንግሥት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው” ብለዋል፡፡ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሠማሩ ባለሀብቶች በበኩላቸው አካባቢው ሠላም መሆን በኢንቨስትመንት ሥራቸው ተጠቃሚ ከመሆናቸው ባሻገር ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንደፈጠሩ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ጎንደር በተለይ ለጋርመንትና ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ምቹ መሆኗን ጠቅሰው ባለሀብቶች በተለያዩ ዘርፎች ቢሰማሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ