“የባሕር ዳር ከተማ አዲስ መዋቅራዊ ፕላን የከተማዋ እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው ፋይዳው የጎላ ነው ” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)

399
“የባሕር ዳር ከተማ አዲስ መዋቅራዊ ፕላን የከተማዋ እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው ፋይዳው የጎላ ነው ” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 27/2013 ዓ.ም (አብመድ) የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
የከተማዋ የመጀመሪያው መዋቅራዊ ፕላን በ1940 ዓ.ም አካባቢ በጀርመን ባለሙያዎች እንደተዘጋጀ ይነገራል፡፡ በ1957 ዓ.ም እና 1980ዎቹ መጨረሻ ላይ ደግሞ የከተማዋ ሁለተኛ እና ሦስተኛ መዋቅራዊ ፕላን ተዘጋጅቶ አገልግሎት ላይ ቆይቷል፡፡
ከግማሽ ሚሊየን በላይ ሕዝብ እንደሚኖርባት የሚነገርላት ባሕር ዳር ከተማ ዘመኑን የዋጀ፣ ዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ እና ሃገር አቀፍ ነባራዊ ሁኔታውን ያገናዘበ እና የቀጣዩን ግማሽ ምዕተ ዓመት የከተሞች ዕድገት ታሳቢ ያደረገ መዋቅራዊ ፕላን ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ የተጀመረው ከሦስት ዓመታት በፊት ነበር፡፡
በ2063 ዓ.ም ከአራት ሚሊየን በላይ ሕዝብ እንደሚኖርባት የተተነበያላት ባሕር ዳር አራተኛው መዋቅራዊ ፕላኗ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አማካኝነት ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ንድፈ ሃሳባዊ ፕላን እና ማስፈፀሚያ እቅዱን አካቶ የያዘው መዋቅራዊ ፕላን የከተማዋን ፀጋዎች፣ መፃዒ የከተሞች ዕድገትን እና የከተማዋን የልማት አጀንዳዎች ታሳቢ አድርጎ መዘጋጀቱ ተጠቁሟል፡፡
በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት የከተማዋ ነዋሪ ሃጂ አሊ ሙሃመድ ኑር መዋቅራዊ ፕላን ለአንድ ከተማ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ከተማዋ የራሷ የሆነ ታሪክ፣ ፀጋ እና ሃብት ያላት በመሆኗ ይህንን ታሳቢ ያደረገ መዋቅራዊ ፕላን ያስፈልጋታል፡፡ የከተማዋ የብዙ ጊዜ ችግር ፍትሃዊ እና ወጥ አሰራር አለመኖሩ ነው ያሉት ሃጂ አሊ መዋቅራዊ ፕላኑ ይህንን ችግር ይቀርፋል ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል፡፡ መዋቅራዊ ፕላኑ የተሻለ ተፈፃሚነት የሚኖረው በየደረጃው ሕዝቡ ሲወያይበት በመሆኑ በቀጣይም በሰፊው ውይይት ሊደረግበት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
መዋቅራዊ ፕላኑ ለከተማዋ ልዩ ትርጉም አለው ያሉት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶክተር) ላለፉት ሦስት ዓመታት ሢሠራ የቆየው የከተማዋ ማስተር ፕላን ወደትግበራ የሚገባበት ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡ በልማት ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት፣ ዘላቂ የመሬት አጠቃቀም ስርዓት ለመዘርጋት እና የከተማዋ እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው መዋቅራዊ ፕላኑ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ነው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የተናገሩት፡፡
ለመዋቅራዊ ፕላኑ ተፈፃሚነት አጋዥ የሆነው ማስፈፀሚያ እቅድ አብሮ መዘጋጀቱን እና የሙከራ ትግበራ መጀመሩን የጠቆሙት ምክትል ከንቲባው ለዘላቂ ትግበራው የባለድርሻ አካላትን እገዛ ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ለመጭዎቹ 50 ዓመታት እንዲያገለግል ታሰቦ የተዘጋጀው የከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን በአምስት የጥናት ቡድን እና ከ90 በላይ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነውበታል፡፡ መዋቅራዊ ፕላኑ የዛሬውን ሳይጨምር አምስት ጊዜ ያህል ሕዝባዊ ውይይት ተደርጎበታል ተብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleሀገር በቀል የግብረ-ገብ፣ የዜግነትና የሰላም እሴቶችን ያካተተ ስርዓተ-ትምህርት ለማዘጋጀት እየተሠራ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
Next articleከ3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በጎንደር ከተማ ኢንቨስት ለማድረግ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡