
ሕዝቡ በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በመርዳት በዓሉን እንዲያሳልፍ ጥሪ ቀረበ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 27/2013 ዓ.ም (አብመድ) ሕዝቡ በሀገሪቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች፣ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝና በተለያዩ ምክንያቶች ኑሯቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ወገኖችን በመርዳት የልደት በዓል እንዲያሳልፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ድርጅት ሊቀመንበር አቶ ኦባንግ ሜቶ ጥሪ አቀረቡ።
አቶ ኦባንግ ከዚህ በፊት በበዓላት ጊዜ ድጋፍ የሚደረገው በአመዛኙ ኑሯቸውን ጎዳና ላይ ላደረጉና ለአቅመ ደካማ አረጋውያን መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በመተከል፣ በደቡብ፣ በኦሮሚያ እና በትግራይ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰቱት ግጭቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ እንዲሁም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ሰዎች በርካታ በመሆናቸው ኅብረተሰቡን ከምንጊዜም በላይ የወገን አለኝታነቱን በመግለፅ የድጋፍ እጁን እንዲዘረጋ ጠይቀዋል።
ኅብረተሰቡ በፖለቲካ አመለካከቱ፣ በዘር፣ በሃይማትና ብሔር ሳይለያይና እንደ ሰው በማሰብ አቅም በፈቀደ መጠን የሚበላ፣ የሚጠጣና የሚለበስ በማቅረብ ለችግር የተጋለጠ ማንኛውም ሰው ሊረዳ እንደሚገባው አመልክተዋል።
ሀገራዊና ወገናዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ጀርመን አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር 220 ሺህ ብር መሰብሰባቸውን አቶ ኦባንግ ጠቁመዋል፡፡
የተሰበሰበው ገንዘብ በግጭት ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች እንደየፍላጎታቸው የተለያዩ አልባሳትና ምግቦች ገዝቶ ለመላክ ፍላጎታቸውን የመለየት ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከሀገር ውስጥም ከተለያዩ ድርጅቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ባለሀብቶች ድጋፎችን ለመሰብሰብ እንቅስቃሴ መጀመራቸውንና የተሰበሰቡ ድጋፎችም ከተፈናቃዮች በተጨማሪ በአዲስ አበባ በችግር ላይ ለሚገኙ ኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሚውል መግለፃቸውን የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት ዘግቧል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ