
የተሰነደው 23 ነጥብ 8 ቢሊየን፤ ወደ ገንዘብ እንዲቀየር ኮሚቴው አሳሰበ።
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 26/2013 ዓ.ም (አብመድ) የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በሰነድ ብቻ ያስቀመጠው 23 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር፤ ወደ ገንዘብ እንዲቀየር የገቢ፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ይህንን ማሳሰቢያ የሰጠው፤ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱን የሥራ እንቅስቃሴ በአካል ከጎበኘ በኋላ አዘጋጅቶ በሰጠው ግብረ-መልስ ነው፡፡ በግብረ-መልሱም በርካታ መስተካከል ያለባቸውን የአሠራር ዕጥረቶች እንዳሉ አመላክቷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ መስፍን መሸሻ ግብረ-መልሱን ባቀረቡበት ወቅት፤ የሚሠሩ እና የማይሠሩ የግዢ እና የሺያጭ መመዝገቢያ ማሽኖች ተለይተው፤ ጥገና፣ ዕድሳት እና ክትትል እንዲደረግላቸው ጠቁመዋል፡፡ የታክስ ማጭበርበርን እና ስወራን በሚመለከትም፤ ክትትል እና ቁጥጥር እንዲደረግ እና ግብር የማያሳውቁ እና የሚያሳንሱ ግብር ከፋዮችን መቆጣጠሩ ተጠናክሮ እንዲቀጠል አሳስበዋል፡፡
በሰነድ የተቀመጠው 23 ነጥብ 8 ቢሊየን ብርም ወደ ገንዘብ እንዲቀየር ከፍተኛ ክትትል እንዲደረግም፤ በቋሚ ኮሚቴው ስም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በሌላ በኩልም፤ ከተጨማሪ ዕሴት ታክስ ማሳወቅ ጋር በተያያዘ ሃምሳ ሁለት ድርጅቶች ያላሳወቁ መሆናቸው፣ 4 መቶ 96 የሺያጭ መመዝገቢያ ማሽኖች በሥራ ላይ አለመሆናቸው እና 1 መቶ 99ኙ ወደ ሥራ የማይመለሱ መሆናቸው፤ በቅርንጫፉ የአሠራር ክፍተትነት ተነስተዋል፡፡
የሺያጭ እና የግዢ መረጃዎችን በመረጃ መረብ የመላክ ስልጠና እና መረጃን ወደ ኮምፒውተር ሥርዓት የመቀየር ተግባር እንዲሁም ለሕጻናት ማቆያ ዝግጅት ትኩረት አለመሰጠቱ በዕጥረት ተጠቅሰዋል፡፡
ኮሚቴው በጥንካሬ ያነሳቸው 87 ነጥብ 5 በመቶ ግብር ከፋይ በኢ-ታክስ ማወቁ እና የውዝፍ ዕዳ አሰባሰብ ከዕቅድ አኳያ የተሻለ መሆኑ ነው፡፡ የታክስ ኦዲትን በሚመለከትም የተሻለ አፈጻጸም መኖሩ፣ እንዲሁም የግዢ ተግባር በዕቅድ መመራቱ፣ አዋጆች እና ሕጎች ተደራሽ እንዲሆኑ መደረጋቸው አበረታች ናቸው ተብሏል፡፡
ከቅርንጫፉ ሠራተኞች ጋር በተደረገ ውይይትም፤ ግብር ከፋዮች በየጊዜው ሶፍትዌሮችን ቀያይረው መጠቀማቸው ክትትል እና ቁጥጥሩን አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው፣ የገቢዎች ሚኒስቴር ሲስተም የዓቅም ውስንነት ሥራዎቻቸውን እንደሚያዘገይባቸው፣ የሲስተም ኦዲት ቢኖር ጥሩ እንደሚሆን፣ የሠራተኛ ምደባ እና ዝውውር ማንዋል መሻሻል እንዳለበት፣ የካፒታል ዕቃዎች ግምታዊ ዋጋ መመሪያ መሻሻል እንዳለበት እና በገንዘብ ሚኒስቴር የሚወጡ ሕጎች የእንግሊዝኛ ቅጂ አለመኖር በአሠራራቸው ላይ ጫና እንዳሳደሩባቸው ገልጸዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው እነዚህን ግምገማዎች ለበላይ አመራር የሚያቀርባቸው መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ የጽህሕፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታሬሳ እንሴሱ እና ሌሎችም ኃላፊዎች፣ የተሰጡ አስተያየቶችን በግብዓትነት ወስደው በቀጣይ ለማስተካከል እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡
የገቢ፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ተገኝቶ የመስክ ምልከታ ማድረጉን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ