በአርቲስት እና አክቲቪስት ታማኝ በየነ የሚመራው የዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት አንድ ሚሊዮን ብር ለተፈናቃዮች ድጋፍ አደረገ።

346
በአርቲስት እና አክቲቪስት ታማኝ በየነ የሚመራው የዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት አንድ ሚሊዮን ብር ለተፈናቃዮች ድጋፍ አደረገ።
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 26/2013 ዓ.ም (አብመድ) ከመተከል ዞን ተፈናቅለው ቻግኒ ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ ተፈናቃዮች በአርቲስት እና አክቲቪስት ታማኝ በየነ የሚመራው ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ከውጭ ሀገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ያሰባሰበውን አንድ ሚሊዮን ብር የምግብ ድጋፍ አድርጓል።
በቻግኒ ከተማ አስተዳደር በመገኘት ድጋፍ ከአደረጉ አሰባሳቢ ኮሚቴዎች መካከል ፕሮፌሰር አቻምየለህ ደበላ እንደገለፁት በመተከል የተፈናቀሉ ወገኖች በችግር ውስጥ መሆናቸውን በመረዳት ወገን ለወገን ደራሽ መሆኑን ለማሳየት በሶስት ቀን የተሰበሰበውን ድጋፍ ይዘው ተገኝተዋል።
የተደረገው ድጋፍ ውስን መሆኑን ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡
የዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት አንድ ሚሊየን ብር የሚገመት ዱቄት እና ዘይት ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው መኖር እስከሚጀምሩ ድረሰ ድጋፉ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
ድጋፉን ይዘው ከመጡት ውስጥ ሌላው አቶ ከፍያለው ፈቃደ ተፈናቃይ እናቶች፣ ህፃናት እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ ተፈናቃዮች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው መደገፍ ይገባቸዋል ብለዋል።
በቀጣይም መንግሥት ዜጎች ወደ ቀያቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ እንዲያመቻችም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ምግብ ዋስትና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽን እታገኘሁ አደመ ለተፈናቃዮች መንግሥት በየጊዜው ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ ቀና አስተሳሰብ ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ በማድረግ ለተቸገሩ ወገኖች እየደረሱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት በውጭ ሀገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከመንግሥት ጎን መሆናቸውን ያሳየበት ወቅት መሆኑን ነው ያስረዱት።
በአማራ ክልል በአሁኑ ወቅት ከ100ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የተናገሩት ወይዘሮ እታገኝሁ የሃይማኖት ተቋማት፣ በጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ዩኒቨርሲቲው ፣ወጣቶች፣የመንግሥት እና የግል ተቋማት፣ባለሃብቶች እና ነዋሪዎች ለተፈናቃዮች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
አብሮነት እና አንድነት የሚረጋገጠው በችግር ወቅት በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለተፈናቃዮች ድጋፍ ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል ምክትል ኮሚሽነሯ።
ዘጋቢ:- አዳሙ ሽባባው- ከቻግኒ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበዜጎች ጭፍጨፋ የሌላ አካል እጂ እንደነበረበት በመተከል ዞን በግድያው የተሳተፉና በቁጥጥር ስር የዋሉ ታጣቂዎች ተናገሩ፡፡
Next articleበኩር ጋዜጣ ታህሳስ 26/2013 ዓ/ም ዕትም