
‹‹መቻሬ ወልዲያ ሳንቃ ደሮ ግብር፣
ያመዋል ሲነካ የራያ ልጅ ክብር
አትንኩት ራያን ድርድር አይወድም
ክብሩን በድርድር አሳልፎ አይሰጥም››
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 25/2013 ዓ.ም (አብመድ) ደግነት እንደ አሸዋ የሚታፈስበት፣ ፍቅር እንደ ዥረት የሚፈስበትና ጀግና የሚወለድበት ነው፡፡ ስሙ ሲነሳ ኩራት ይሰማል፣ ሳያውቁት ይናፈቃል፣ ሲያዩት ልብን በፍቅር ይሰርቃል፡፡ ማር ቢሉ ወተት፣ ቢፈልጉ ጤፍ እንጀራ ቢያሻዎት ከልቡ የኮራ ጀግና ያኙበታል በራያ ምድር፤ በራያ አጀብ የሚያሰኝ ውበት፣ አበጀህ የሚያሰኝ ጀግንነት፣ የማይናወጥ ኢትዮጵያዊነት አለ፡፡ ራያን የረገጠ ሁሉ መንፈሱ ሀሴትን ታገኛለች፡፡

የሚያቋት ‹‹በኮለምላማ›› ዜማ ራያን ይቃኟት ይጀምራሉ፡፡ የማያውቋት ደግሞ ሊያዩዋትና ሊያውቋት ይመኛሉ፤ ኑርአዲስ ሰይድ ( ጃሪጋማ)፡፡
ኑርአዲስ ሰይድ በግፈኛው ትህነግ በተወለዳባት የራያ ምድር እንደ አሻው እንዳይሆን፣ በሚወዳት የትውልድ ቀዬው ጃሮታጋማ የሚገኙ ቤተሰቦቹን እንዳያይ ተከልክሎ ቆይቷል፡፡ በዋጃ አቅራቢያ ጃሮታጋማ የተወለደው ኑርአዲስ በአላማጣ ከተማ ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡ የጥበብ ሥራን የጀመረውም በአላማጣ ከተማ እርሱና ጓደኞቹ ባቋቋሙት በትግሥት ባንድ ነበር፡፡ በትግሥት ባንድ በነበረበት ጊዜ በፍቅር ይሰሩ እንደበር ነግሮናል፡፡ ነገር ግን ትህነግ የሚፈልጉትን ነገር እንዳይሰሩ ያስገድዷቸው እንደነበርም ያስታውሳል፡፡
እርሱ ከትግሥት ባንድ ወጥቶ ከሄደ በኃላም በትግሥት ባንድ አባላት ላይ ጫና ይደርስባቸው እንደነበርና ከአካባቢያቸው ለመሠደድ እንደተገደዱም ነግሮናል፡፡
ኑርአዲስ ተደማጭነቱ ከፍ እያለ ሲሄድና ነጠላ ዜማዎችን መልቀቅ ሲጀምር የትህነግ ሰዎች ያጠምዱት ጀመር፡፡ አላማጣ መግባት ህልም እየሆነበት መጣ፡፡ እነርሱም ያሳድዱት ጀመር፡፡ የኑርአዲስን ዘፈን ተሽከርካሪው ላይ፣ መጠጥ ቤቶችና በሌሎች አጋጣሚዎች የከፈተ ሁሉ ይታሰርና ይንገላታ ጀመር፡፡ በመጠጥ ቤት ዘፈኑን የከፈቱ የቤቱ ባለቤት ብቻ ሳይሆን ለተዝናኖት የመጡ ሰዎችም የእንግልቱ ተካፋይ ነበሩ፡፡ ኑርአዲስ አላማጣ መግባት ባይችልም ‹‹በለው በወንጭፉ›› እያለ ትግሉን ቀጠለ፡፡
‹‹ኢቦ ወዲህ ማዶ አላህዋ መላሽ፣ ወሰን አስከባሪ አለ ብዙ ተኳሽ›› የኑርአዲስ ሥራዎች ከፍ እያሉ ሄዱ፡፡
ከራያም አልፎ የወልቃይትን ጥያቄ የሚያጠናከር ዜማ ‹‹አልተዘጋም ዶሴው›› ሲል አዜመ፡፡ ‹‹እኛ የሚመስለንን ሆነን አይደለም ያለነው፤ ወደሚመስለን መመለስ አለብን›› የሚል ጥያቄ እንደነበራቸውም ነግሮናል፡፡ ራያና ወልቃይት የሚመስለውን ለማግኜት በርካታ የጭቆና ጊዜያትን አሳልፏል ነው ያለን፡፡ ‹‹ራያ ማለት ወሎ ነው፣ ወሎ አማራ ነው›› ያለው ድምጻዊ ኑርአዲስ ‹‹ስማ በለው ወልቃይት ጎንደር ነው፣ ቃፍታ የአማራ ነው›› ሲልም በጉልበት የወሰዱትን ሰዎች በዜማ ነግሯቸዋል፡፡ አሁን ላይ በጀግኖች ታግዞ ጥያቄየ ተመልሶልኛል ብሏል፡፡
የራያን ባሕል ለማስተዋወቅ ሢሠሩ የተበረዘ ነገር እንዲሆንና እየተበረዘ እንዲጠፋ ጫና ያድርባቸው እንደበርም ኑርአዲስ ነግሮናል፡፡ የራያ ባሕል እንዳያድግ ትህነግ ይሠራ እንደነበርም አስታውሷል፡፡
ኑርአዲስ ከዓመታት በኋላ ወደ ሚወዳትና ከልቡ ወደ ማትጠፋው የራያ ምድር አላማጣ ከተማ ሲገባ‹‹ በጣም ነው ደስ ያለኝ እንደገና የተወለድኩ ያክል ነው የተሰማኝ፣ ምክንያቱም የተወለዱበት ሀገር ላይ መግባት ሲከለከል፣ ቤተሰብ ጋር መገናኛት ሳይቻል ሲቀር፣ በቤተሰብ ላይ ዛቻ እየተዛተ፣ ያ ሁሉ አልፎ በነጻነት መግባት ደስታው ወደር የለውም›› ነው ያለው፡፡ ኑርአዲስ ከዓመታት ቆይታ በኋላ በራያ አላማጣ ከሚወዱትና ከሚወዳቸው ራያዎች ጋር ‹‹በላለይ ጉማ›› ደምቋል፡፡ በርቀት ያሰቃየውን የራያ ልጅ ፍቅር ቀርቦ አጣጥሞታል፡፡
ሰው ወዳዱን፣ እንግዳ ተቀባዩን ደጉን የራያን ሰው በማንነቱ እንዳይኖር ሲያደረጉ መቆየታቸውንም ኑርአዲስ ነግሮናል፡፡ ኑርአዲስ በፍቅር ዘፈን አስመስሎ ስለ ራያ እንዲህ ሲል ተጫውቷል፤

እስኪ እነነጋር፣
ስሞታ አለኝ ስጋት ያስገባኝ
ነይ እንገናኝ፤
እናትና አባትሽ ከእኔ ሌላ ሊድሩሽ ነው አሉ
ፍቅር በልባችን ተጠንስሶ እያለ በቃሉ፤
በአንቺማ የመጣ እንቅልፍ የለኝ በከንፈር ወዳጄ
እንዴት አሳልፌ ዓይኔ እያዬ ይወስዱሻል ከእጄ
…. በሕይወት እያለሁ ቆሜ ሳልሞት ገና
አንቺን የሚወስድሽ እንዬው እስኪ ማነው ጀግና››
ኑር አዲስ ትህነግ እየለቀቀ ሲሄድ “ጁንታው መሸበት” የሚል ነጣላ ዜማም ለሕዝብ አድርሷል፡፡
‹‹እንደመሸ አልቀረም እንደጨለመብን፤
የእነርሱንም ጣሉት እንኳን ሊወስዱብን፣
ሃያ ሰባት ዓመት ኑሬ ሳስታምመው፣
እኔንም ደከመኝ እሱም አልተሻለው›› በማለት ያሰቡት ሁሉ እንዳልተሳካቸውና በዓመታት ሂደት ውስጥ የተሻለ አካሄድ እንዳላሳዩ ነግሯቸዋል፡፡
በራያ ሕዝብ ጥያቄና በሚገልጸው ሃሳብ የሚደርሰውን ጫና ፈርቶ ለመመለስ አንድም ቀን አስቦ እንደማያውቅ ነው ኑርአዲስ የተናገረው፡፡ እርሱ የተወለደባት ዋጃና አካባቢዋ በትህነግ እጅ ስለነበረች ቤተሰቦቹን እንደ ማንኛውም የራያ ሕዝብ በማሰብ እነርሱን አስይዞ ሲታገል እንደነበርም ነው የነገረን፡፡ የራያ ሕዝብ ከዚያ ሁሉ አፈና ተላቆ ማየቱ ትግሉ ስኬታማ መሆኑንም ገልጾልናል፡፡
የራያ ሕዝብ ባሕሉንና ወጉን ጠባቂ ነው ያለው ኑርአዲስ የራያ ባሕልና ወግ እንዲያድግ የባሕል ማዕከል እንዲገነባም ጠይቋል፡፡ ማኅበረሰቡም ተረጋግቶ ራሱን ከሚመስለው ጋር መኖር አለበት ነው ያለው፡፡ ደፊትም በሙያው የራያን ሕዝብ ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
‹‹ አርባ ዙር ነው ድጉ ብትሩ መዋጣ
ወሎ ነው አምሳያው የራያ አላማጣ
ምድር ብትናጥ ሰማይ ዝቅ ቢል
የለም አንዳቻ ራያን ከወሎ ችሎ ሚነጥል›› ሲልም ተቀኝቷል፡፡ ሂዱ ከራያ ፍቅር ቅመሱ፣ በደግነታቸው መንፈሳችሁን አድሱ፣ በራያ ምድር የፍቅር አዝመራ አይታጣም፣ በራያ መተባበር፣ መተሳሰብና መልካምነት ሞልቷል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ