
“ሰሞኑን የሱዳን ኀይሎች ኀላፊነት በጎደለው መልኩ የኢትዮጵያን መሬት መያዛቸው ስህተት እንደሆነ፤ አንዳንድ የሱዳን ሚዲዎችና ባለስልጣናትም መሬታቸውን እንዳስመለሱ አድረገው በመግለጫ የሚያሰራጩት መረጃ ተቀባይነት የለውም” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 25/2013 ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮ ሱዳን ድንበር ግጭት ሱዳን መንግሥትና ሰፊው የሱዳን ሕዝብ ፍላጎት እንዳልሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታወቁ። ግጭቱ ለማንም እንደማይበጅ የኢትዮጵያ አቋም መሆኑንም አመላክተዋል።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በግጭቱ ዙሪያ እንዳስታወቁት፣ የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር 100 ዓመት ያስቆጠረ ቢሆንም በሌሎችም የአፍሪካ አገራት እንደሚታየው ከቅኝ ገዥዎች የተወረሱ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በቅኝ ገዥዎች ባትገዛም ሱዳን በቅኝ ግዥዎች ስር ስለነበረች፣ ድንበሩ ምንም እንኳ ምልክቶች ቢኖሩትም በዘመናዊ ዘዴ በትክክል ባለመካለሉ አንዳንዴ በሁለቱም ሀገራት የድንበር አካባቢዎች መገፋፋቶች ይፈጠራሉ ብለዋል፡፡
አሁን ያለው ድንበር ባህላዊ መሆኑን ጠቁመው፣ ሰሞኑን የሱዳን ኀይሎች ኀላፊነት በጎደለው መልኩ የኢትዮጵያን መሬት መያዛቸው ስህተት መሆኑ እንዳለ ሆኖ አንዳንድ የሱዳን ሚዲዎችና ባለስልጣናት መሬታቸውን እንዳስመለሱ አድረገው በመግለጫ የሚያሰራጩት መረጃ ተቀባይነት የሌለውና ህገ ወጥ መሆኑ አስታውቀዋል።
አንዳንድ የሱዳን ባለስልጣናት ከኋላ ሆነዉ ጉዳዩን ለሚያቀጣጥሉ የኢትዮጵያ ጠላቶች መጠቀሚያ ሆነው ቢያገለግሉም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ግጭቱ የሱዳን ሕዝብና መንግሥት ፍላጎት ነው የሚል መደምደሚያ ላይ እንዳልደረሰ ገልጸዋል።
ይልቁንስ መጠቀሚያ እየሆኑ ያሉ የሱዳን ባለስልጣናት ድርጊታቸው ሱዳንንም ሆነ ኢትዮጵያን በፍጹም ስለማይጠቅም ያሉትን ችግሮች በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ የኢትዮጵያ መንግሥት እያሳሰበ መሆኑን ገልጸዋል። ድንበሩም በድንበር ኮሚሽን መርሆዎች ብቻ እንዲፈታም የኢትዮጵያ አቋም እንደሆነም አስታውቀዋል።
ግጭቱ የሱዳን መንግሥትና የሱዳን ሕዝብ ፍላጎት እንዳልሆነ የሚገልጹ “እኛ ከኢትዮጵያ ጋር ፈጽሞ ወደ ግጭት አንገባም” የሚሉ ድምፆች እየጨሩ መምጣታቸውን የጠቆሙት አምባሳደር ዲና፣ ከበስተጀረባው ግን የተለያዩ ኃይሎች እንዳሉ ጠቁመዋል።
እነዚህ ኃይሎች ለዘመናት ያልጠቀሟትን ሱዳን ወዳጅ በማስመሰል የጥፋት አጀንዳቸውን ለማሳካት እየታተሩ እንደሚገኙ ጠቁመው ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሠላም ወዳዱ የሱዳን ሕዝብ እና ባለስልጣናት፣ እንዲሁም ለሰላም ወዳዱ የአረቡ ማህበረሰብ ፣ ግጭቱ ለማንም እንደማይበጅ በተጨባጭ እያሳወቀች መሆኑን አመልክተዋል።
አምባሳደሩ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት አንዳንድ የሱዳን ወታደሮችና ሚሊሻዎች ሰሞኑን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በመግባት የሰው ህይወት ማጥፋታቸውና ንብረት ማውደማቸውን አመልክተው፣ መንግሥትም ጸጥታን ከማስከበር ጎን ለጎን ችግሩ በድርድር እንዲፈታ እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ