
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱ ዙሪያ እየመከረ ነው፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 24/2013 ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተፈጥሮ ሃብት፣ መስኖና ኢነርጂ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱ ዙሪያ ዛሬ በአዳማ ከተማ የምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ እንደተናገሩት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለሀገራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት ስኬት እያበረከተ ያለው አስተዋፆ ከፍተኛ ነው፡፡
ተቋሙ አስተማማኝ፣ ፍትሀዊና ተደራሽ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ ለማስፈን ሰፊ የለውጥ ሥራዎች ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግና ሀገራዊ የኤሌክትሪክ ሽፋንን ለማሳደግ “የብርሀን ለሁሉ” መርኃ ግብር ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2025 65 በመቶ የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ከብሔራዊ የኤሌክትሪክ ቋት እንዲሁም 35 በመቶው ደግሞ ከብሔራዊ የኤሌክትሪክ ቋት ውጪ ወይም በኦፍ ግሪድ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ የውስጥ አሠራሩን ለማዘመን እየሠራ መሆኑን ያመላከቱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ የኃይል ማከፋፈል መልሶ ግንባታና አቅም የማሳደግ ሥራዎች መተግበራቸው አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግና የውስጥ አሰራርን ለማዘመን ማገዙን አመላክተዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈፃሚው አክለውም የደንበኞች የመክፈል አቅም ታሳቢ ባደረገና ፍትሀዊነትን ባረጋገጠ መልኩ ከ2011 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም በየዓመቱ ተከፋፍሎ ተግባራዊ የሚደረግ የታሪፍ ማስተካከያ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተግባራዊ መደረጉን አስታውሰው፤ በተያዘው ወርም የማስተካከያው ሶስተኛው ዙር እንደሚተገበር ጠቁመዋል፡፡
የፋይናንስ ዕጥረት፣ የግብዓት አቅርቦት ችግር፣ የኢነርጂ ብክነትና ስርቆት፣ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ የሚደርሱ ስርቆቶችና አደጋዎች፣ የኃይል ማከፋፊያ ኔትዎርኩ በማርጀቱ ለኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ እንዲሁም ለመልካም አስተዳደር ችግር መንስኤ እየሆነ መምጣቱ የተቋሙ ማነቆዎች መሆናቸውን መግለፃቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ