ነዋሪነታቸውን በአሜሪካ ያደረጉት ዶክተር አስረሱ ምስክር ለእምቦጭ አረም ማስወገድ ዘመቻ የ800 ሺህ ብር ቁሳቁሶችን ለገሱ፡፡

217
ነዋሪነታቸውን በአሜሪካ ያደረጉት ዶክተር አስረሱ ምስክር ለእምቦጭ አረም ማስወገድ ዘመቻ የ800 ሺህ ብር ቁሳቁሶችን ለገሱ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 24/2013 ዓ.ም (አብመድ) አሜሪካ የሚኖሩ በጎ አድራጊ ዶክተር አስረሱ ምስክር እምቦጭን ለማስወገድ እየተሳተፉ ላሉ አርሶአደሮች የሚውል ግምታቸው 800 ሺህ ብር የሆነ አልባሳትና የጽዳት ቁሳቁሶችን ለገሱ፡፡
የጣና ሐይቅና ሌሎች የውኃ አካላት ኤጀንሲ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ልየው እንደገለጹት የጎንደር አካባቢ ተወላጅ የሆኑት ዶክተር አስረሱ ካስረከቡዋቸው ቁሳቁሶች መካከል የእምቦጭ አረም ለማስወገድ የሚውል 300 አልባሳት ይገኝበታል፡፡ 500 የእጅ ጓንቶችና ከ2ሺህ በላይ የግል ንጽህና መጠበቂያ ሳሙና እንደተለገሰም ገልጸዋል።
አልባሳቱና የእጅ ጓንቶቹ ከጣና ሐይቅ ላይ አረሙን በእጃቸው የሚያስወግዱ አርሶአደሮች እንዳይጎዱ ለመከላከያነት የሚያገለግሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ዶክተር አስረሱ ምስክር ተወካይ አቶ ሚሊኪያስ ታዬ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጣና ሐይቅ አዋሳኝ በሆነው ሸሃ ጎመንጌ ቀበሌ በመገኘት ድጋፉን በኤጀንሲው በኩል በአረም ማስወገድ ዘመቻው ለተሳተፉ አርሶ አደሮች አስረክበዋል፡፡
ተወካዩ እንደተናገሩት በአሜሪካ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች በሐይቁ አካባቢ ለሚኖሩ የአርሶአደሩ ልጆች ትምህርት ቤት ለመገንባት እቅድ እንዳላቸው ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
ሐይቁን የወረረውን አረም በማስወገድ በጉልበታቸው መሳተፍ ከጀመሩ ስምንት ዓመት ማስቆጠራቸውን የተናገሩት ደግሞ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የሸሃ ጎመንጌ ቀበሌ አርሶአደር ካሳው ታግሎ ናቸው፡፡
“ሐይቁ ውስጥ ገብተን አረሙን በምናስወግድበት ወቅት በእባብና በሌሎችም ነፍሳት ጉዳት ሲደርስብን ቆይቷል” ያሉት አርሶአደሩ የተሰጣቸው ቁሳቁስ ችግሩን ለማቃለል እንደሚረዳቸው ተናግረዋል፡፡
ሌላዋ ነዋሪ ወይዘሮ ትዛሉ ተገኘ የተደረገላቸው አልባሳት ድጋፍ በእጅና እግራቸው ላይ ሲደርስባቸው የነበረውን ችግር ለመፍታት እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።
ለሁለት ወራት በዘለቀው ሀገር አቀፍ የእምቦጭ አረም ማስወገድ ዘመቻ ስኬታማነትም የፌደራልና ክልል መንግስታዊ ተቋማት እስካሁን ድረስ 30 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ከጣና ሐይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleማንነትን መሰረት ያደረገ ምጣኔ ሀብታዊ መድሎ እና መገለል – በጠለምት ጥቁር ውኃ ከተማ
Next articleየኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱ ዙሪያ እየመከረ ነው፡፡