
ማንነትን መሰረት ያደረገ ምጣኔ ሀብታዊ መድሎ እና መገለል – በጠለምት ጥቁር ውኃ ከተማ
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 23/2013 ዓ.ም (አብመድ) ትህነግ ገና ለትግል ወደጫካ ሲገባ ጀምሮ ድብቅ የትግል ዓላማው እና መስመሩ አማራ ጠል የሀሰት ትርክት ላይ የተመሰረተ እንደነበር ማኒፌስቶው በግልፅ ያሳያል፡፡
የአማራ ሕዝብ ከቀሪ ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹ ጋር ግንባሩን ለአረር፣ ደረቱን ለጦር እና እግሩን ለጠጠር ሰጥቶ በፍፁም ሀገራዊ ተቆርቋሪነት ድንበር ለማስከበር በሁሉም አካባቢዎች ዱካው ያረፈ ነው፡፡ ይህ እውነት እየታወቀ ትህነግ በድብቅ ማኒፌስቶው ለትግራይ ሕዝብ ጉስቁልና አማራን ምክንያት አድርጎ ማቅረቡ የትህነግን አማራ-ጠል ትርክት በግልፅ ያመላክታል፡፡
ከ17 ዓመታት የትጥቅ ትግል በኋላ በኢትዮጵያ ሕዝብ ደም በ1983 ዓ.ም ወደስልጣን የመጣው ትህነግ ሕገ መንግሥቱ ከመፅደቁ ቀድሞ ከፈፀማቸው የፖለቲካ ሴራዎች መካከል አንዱ ነባሩን የአማራ ርስት ሸንሽኖ ማከፋፈል ነበር፡፡
በዚህም በርካታ ቀደምት የአማራ ርስቶች ያለሕዝቡ ፍላጎት ወደትግራይ እንዲካለሉ ተደረገ፡፡ ማንነታቸውን የጠየቁ ለእስር እና ስደት፤ አምርረው የታገሉ ደግሞ የደረሱበት እንዳይታዎቅ ተደርገው እንደተሰወሩ በርካቶች ይናገራሉ፡፡ ከዚህ መሰል ስቃይ የተረፉት ደግሞ ማንነታቸው እየተለየ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኀበራዊ መገለል እና መድሎ ይፈፀምባቸው እንደነበር ይገልጻሉ፡፡
አቶ ግደይ ተክሌ ከልጅነት እስከ እውቀት ነዋሪነታቸው እና ትውልዳቸው ጠለምት ጥቁር ውኃ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ በንግድ ሥራ ኑሯቸውን የሚመሩት እና ቤተሰብ የሚያስተዳደሩት አቶ ግደይ ለቀደምት ማንነታቸው ያደላሉ በሚል ሰበብ ምጣኔ ሀብታዊ በደል እና ጭቆና ይፈፀምባቸው እንደነበር አጫውተውናል፡፡ ከስሚንቶ እስከ ቢራ ማከፋፈያ የተለያዩ የንግድ መስኮችን ቢሞክሩም በየዓመቱ በሚጣልባቸው ፍትሐዊ ያልሆነ ግብር ከንግድ መስመሩ ተገፍተው እንዲወጡ ተደጋጋሚ ጫና ተፈጠረባቸው፡፡
በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ግብር ሲጣልባቸው ፍትሐዊ እንዳልሆነ ቢያውቁትም ግብር አይቀሬ እዳ ነው በሚል የከፈሉት አቶ ግደይ ከክፍያ በኋላ የተጣለባቸው ከ800 ሺህ ብር በላይ ተጨማሪ ግብር ግን ሥራ እንዲያቆሙ አስገደዳቸው፡፡
የንግድ ሥራውን አቁመው ክርክር የጀመሩት አቶ ግደይ ሥራ መሥራት የማልችል ከሆነ በሚል 170 ሺህ ብር ቤታቸውን ለመሸጥ ከገዥ ጋር ተስማምተው ከጨረሱ በኋላ ውሉን ሕጋዊ ለማድረግ ቴምብር ለመግዛት ሲሄዱ ግን ቤታቸው እንዳይሸጥ እና እንዳይለወጥ ማገጃ እንደወጣበት ተነገራቸው፡፡
ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለአራት ዓመታት ቤቴ በትህነግ ትዕዛዝ ብቻ ታግዶ ቆየ የሚሉት አቶ ግደይ ብድር አውጥተው ሥራ እንዳይቀይሩ ብድር ተከለከሉ፡፡
ከተለያዩ አካባቢዎች ጠለምትን ለመምራት የሚመጡት ሹማምንት ተራ በተራ በአካባቢው ነባር ነዋሪዎች ላይ የከፋ መገለል እና መድሎ ይፈፅሙባቸው እንደነበርም ነው አቶ ግደይ የተናገሩት፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጭ አቶ አዳነ ቢተውልኝ የጠለምት ነዋሪ ናቸው፡፡ በተደጋጋሚ በትህነግ ሰዎች በደል እና ጭቆና ይደርስባቸው እንደነበርም ነግረውናል፡፡
በጥቁር ውኃ ከተማ የእርሳቸው እና የቤተሰቦቻቸው ቦታ እንደነበራቸው የሚናገሩት አቶ አዳነ ቦታው ለልማት ይፈለጋል በሚል 60 ሺህ ብር ካሳ ተሰጥቷቸው እንዲነሱ ከተደረገ በኋላ ከ10 ሚሊየን ብር በላይ በሊዝ ተሸጠ፡፡ ከከተማዋ በቅርብ ርቀት የሚገኝ ሌላ የእርሻ ቦታቸው ደግሞ ለጥናት እና ምርምር ይፈለጋል በሚል ሰበብ ያለትክ ለ17 ዓመታት ተነጥቀዋል፡፡
ለ11 ዓመታት ከጥቁር ውኃ እስከ ሽሬ፤ ከመቀሌ እስከ አዲስ አበባ በክስ የቆዩት አቶ አዳነ በይግባኝ ቢፈረድልኝ እንኳን ከእነርሱ ወገን ስላልሆንኩ ተፈፃሚ አልተደረገልኝም ይላሉ፡፡ በዚህ መልኩ ከመኖሪያ እና ከእርሻ ቦታቸው የተፈናቀሉ በርካታ ሰዎች መኖራቸውንም ነው አቶ አዳነ የነገሩን፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከጠለምት ጥቁር ውኃ ከተማ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ