
የአማራ ልማት ማሕበር (አልማ) ለአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጂት ዘመናዊ የምስልና ድምፅ ካሜራ በሽልማት አበረከተ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 22/2013 ዓ.ም (አብመድ) አልማ በአማራ ክልል ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያከናውናቸው ማኅበራዊ መሠረተ ልማቶች ዙሪያ ከአጋር አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
አልማ እንዳስታወቀው የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያከናውነው ሥራ የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጂት ድጋፉ ከፍተኛ ነው፡፡ ድርጂቱ ላከናወነው ሥራም ዘመናዊ የምስልና ድምፅ ካሜራ ከእነሙሉ መሳሪያዎቹ በሽልማት አበርክቷል፡፡
የአልማ የሕዝብ ግንኙነትና የኮምዩኒኬሽን ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አዲሱ ምክሩየ የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጂት አልማ እ.አ.አ ከ2012 ጀምሮ እስከ 2014 ለአቀደው የ3 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ መሳካት ሰፊ የዘገባ ሽፋን በመስጠት አጋርነቱን አሳይቷል፤ በዚህ ምክንያትም ሽልማቱ ተበርክቶለታል ብለዋል፡፡

ለአብነት አልማ በክልሉ የዳስ ትምሕርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ በሠራው ሥራ የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጂት አስተዋጾ ከፍተኛ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
የድርጂቱ ሠራተኞች የአልማ አባል ሆነው ከደሞዛቸው ድጋፍ በማድረግም የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጂት በክልሉ ቀዳሚ መሆኑንም አቶ አዲሱ አብራርተዋል፡፡
በሀገራዊ ለውጡ ከፍተኛ ድርሻ በመወጣት ላይ ሚገኘው የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጂት በክልሉ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን በማገዝ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ እዲቀጥልም በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡
ዘጋቢ፡- ሸምስያ በሪሁን
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ