
ኢንጀንደር ሄልዝ ኢትዮጵያ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ለአማራ ክልል ጤና ቢሮ ድጋፍ አደረገ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 22/2013 ዓ.ም (አብመድ) ኢንጀንደር ሄልዝ ኢትዮጵያ 8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ለአማራ ክልል ጤና ቢሮ ድጋፍ ማድረጉን በኢትዮጵያ የድርጅቱ ተወካይ አቶ ጀማል ካሳው ተናግረዋል።
ድጋፉ የሥነ ተዋልዶ ጤናን ተደራሽነት ለማሳደግ፣ የእናቶችን የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት፣ የወጣቶችንና ሌሎችን የኅብረተሰብ ክፍሎች ጤናን ለመጠበቅ የሚያግዝ እንደሆነ አቶ ጀማል አስረድተዋል። “ድጋፉ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም” ያሉት ተወካዩ የኮሮናቫይረስ እንደተከሰተ የ600ሺህ ብር ቁሳቁስ እንዲሁም ወረርሽኙን ለመከላከል የ3 ሚሊዮን ብር ቁሳቁስ መርዳታቸዉን አስታውሰዋል።
አቶ ጀማል አሁን ደግሞ ለተለያዩ ህክምና የሚያገለግሉ የ8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። የማዋለጃና ለምርመራ የሚውሉ አልጋዎች፣ የአልትራሳዉንድና ስቴቴስኮፕ ቁሳቁስ በድጋፍ ከተበረከቱት መካከል ይጠቀሳሉ።
ድጋፍ የተደረገው ቀድሞ የህክምና ቁሳቁስ እጥረት መኖሩን በጥናት በመለየት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጀማል ወደፊትም የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ታሪኩ በላቸው ድጋፉን ተረክበዋል። ድጋፉን ለማድረግ ከአንድ ዓመት በፊት የክልሉ ጤና ቢሮና ኢንጀንደር ሄልዝ ኢትዮጵያ በጋራ ሆነው ባደረጉት የሆስፒታልና የጤና ጣቢያ ጉብኝት ያጋጠሙትን ክፍተቶች በመለየት እንደሆነ አቶ ታሪኩ አስገንዝበዋል።
በድጋፍ የተገኙት ቁሳቁስ በክልሉ ፕሮጀክቱ በሚንቀሳቀስበት አካባቢ ለሚገኙ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች መሆኑንም ምክትል ኀላፊው ተናግረዋል። በአማራ በክልሉ ጤና ቢሮ ሥምም ለድርጅቱ አቶ ታሪኩ ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ