
ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ በኢንቨስትመንት የ 2 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ተጠቃሚ ሊሆኑ ነው፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሥሥ 22/2013 ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ የንግድ ማነቃቃትን ካለመው እና የአሜሪካ መንግሥት ኤጄንሲ ከመደበው 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ኢንቨስትመንት ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
በአፍሪካ፣ በምሥራቅ አውሮፓ፣ በኢንዶ-ፓስፊክ፣ በላቲን አሜሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት እየተነቃቃ ላለው ንግድ ዓለም አቀፍ ልማት የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (ዲ.ኤፍ.ሲ) ኢንቨስትመንቱን ማጽደቁ ተገልጿል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት የበይነ መረብ ግንኙነትን ለማሳደግ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን ኔትወርክ እና የመረጃ ማዕከላትን ለመገንባት 800 ሚሊዮን ዶላር ይሰጣል ፡፡ በምስራቅ አፍሪካ ዲ.ኤፍ.ሲ በቮዳፎን ለሚመራው ዓለም አቀፍ አጋርነት ለኢትዮጵያ አዲስ የግል የሞባይል ኔትወርክ አቅራቢ ዲዛይን ፣ ልማትና አሠራር ላይ ፈቃድ ለማግኘት 500 ሚሊዮን ዶላር ብድር ይሰጣል ተብሏል፡፡
ፕሮጀክቱ አስተማማኝ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በኢትዮጵያ ውስጥ በዘርፉ ያለውን ግንኙነት ከፍ የሚያደርግ አዲስ የግል ቴሌኮሙኒኬሽን መረብ ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዓለም አቀፍ ልማት የፋይናንስ ኮርፖሬሽን በደቡብ አፍሪካ እና በኬንያ ያሉ ነባር የመረጃ ማዕከል ሀብቶችን በማሻሻልና በማስፋፋት በመላው አፍሪካ በ 300 ሚሊዮን ዶላር የመረጃ ማዕከላት ልማት ድጋፍ ያደርጋል ነው የተባለው፡፡ ይህም ሀገራቱ ወደ አዳዲስ ገበያዎች ለመግባት ያስችላቸዋል፤ ግንኙነቱን ያሳድጋል እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ልማታቸውን እንደሚደግፍ ተመላክቷል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አደም ቦለር በሰጡት መግለጫ የዲ.ኤፍ.ሲ የዳይሬክተሮች ቦርድ በስድስት ፕሮጀክቶች ውስጥ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር አጽድቋል፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው መግለጫ በዚህ ሩብ ዓመት ከፀደቀው የዲኤፍሲ በጀት ውስጥ ከ65 በመቶ በላይ የሚሆነው ወደ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገሮች ፈሰስ ይደረጋል፡፡
ኢንቨስትመንቶቹ አነስተኛ ንግዶችን ያጠናክራሉ፣ ሴት ሥራ ፈጣሪዎችንም ይደግፋሉ፣ ቴሌኮሙኒኬሽንን ያስፋፋሉ እንዲሁም ንግዱን ያነቃቃሉ ማለታቸውን ዘ ኢስት አፍሪካን ዘግቧል፡፡
በየማነብርሃን ጌታቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ