
“ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከአርባ ዓመታት በላይ በእቅድ፣በስልጠና እና በበጀት የተሸረበውን ሴራ መመከት የሚቻለው አንዱ ለአንዱ ጋሻና መከታ በመሆን እንጂ አንዱ ሌላውን እንደ ጠላት በማየት አይደለም” የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 21/2013 ዓ.ም (አብመድ) የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን የፌደራል መንግሥትን በመወከል ከመተከል ዞን ተፈናቅለው በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ልዩ ልዩ የምግብ ዓይነቶችንና የአልባሳት ድጋፍ አድርጓል፡፡
በድጋፉ ወቅት በቻግኒ ከተማ አስተዳደር ራንች በሚባል ቦታ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮችንም የገቢዎች ሚኒስትሩ ላቀ አያሌው፣ የአማራ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳደር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተው ጠይቀዋቸዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥት እንዲህ ዓይነት ችግር ሲደረስ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማት በሰጠው አቅጣጫ ለተፈናቃዮች ድጋፍ ይዘው በቦታው መገኘታቸውንም የገቢዎች ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ወቅትም “ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከአርባ ዓመታት በላይ በእቅድ፣በስልጠና እና በበጀት የተሸረበውን ሴራ መመከት የሚቻለው አንዱ ለአንዱ ጋሻና መከታ በመሆን እንጂ አንዱ ሌላውን እንደ ጠላት በማየት አይደለም” ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
አንዱ ከአንዱ ጋር እንዳይኖር፣ ሞት እና መፈናቀል እንዲደርስ በመደረጉ በጉዳዩ የፌደራል መንግሥት፣የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የጉምሩክ ኮሚሽን ተጠሪ ተቋማት እና የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር አመራሮች እና ሠራተኞች ከልብ ማዘናቸውን ገለጸዋል፡፡
አንዱ ብሔር ለሌላው ብሔር መከታ እና አጋር እንዳይሆን በመሠራቱ ለዘመናት አብሮ የኖረው ሕዝብ በጋራ እንዳይኖር እና የንጹሓን ሕይወት እንዲጠፋ አድርጓል ነው ያሉት ሚኒስትሩ፡፡ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በመሆን ለሀገሪቱ ህልውና ዋጋ ለከፈለው አማራ ይህ እንደማይገባውም ጠቅሰዋል፡፡ ዜጎች እንዲሞቱና እንዲፈናቀሉ የሚያደርጉትን ሁሉም በጋራ ሊመክተው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው- ከቻግኒ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ