
በቻግኒ ከተማ አስተዳደር ራንች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች የመድኃኒት ድጋፍ እንዲቀርብ ጠየቁ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሥሥ 21/2013 ዓ.ም (አብመድ) ከመተከል ዞን ተፈናቅለው በቻግኒ ከተማ አስተዳደር ራንች መጠለያ ጣቢያ የሰፈሩ ተፈናቃዮች ከመንግሥት የጤና ተቋማት የማያገኙትን መድኃኒት በግል ገዝተው ለመጠቀም ባለመቻላቸው መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ ጦቢያው ጓንጉል ከመተከል ዞን ተፈናቅለው በቻግኒ ከተማ አስተዳደር ራንች በተባለ ጊዜያዊ መጠለያ ይገኛሉ፡፡ ወይዘሮ ጦቢያው የስኳር ህመም ታማሚ በመሆናቸው ወደ ጤና ጣቢያ ሄደው በነፃ ሙሉ የምርመራ አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
ምርመራውን አጠናቀው እንደወጡ መድኃኒት በጤና ተቋም ማግኘት ባለመቻላቸው ከግል ገዝተው እንዳይጠቀሙ የተፈናቀሉት ባዶ እጃቸውን በመሆኑ በሐኪም የታዘዘላቸውን መድኃኒት አለመውሰዳቸው ለጤና ችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ ጦቢያው በመጠለያ ጣቢያው የመድኃኒት አቅርቦት አለመኖሩ ሞት እዚህም ተከትሎአቸው እንደመጣ ያህል እየተሰማቸው ነው። በመንግሥት የጤና ተቋማት ከምርመራ አገልግሎት በተጨማሪ መድኃኒት ሊቀርብላቸው እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡
የተፈናቃዮች የጤና ኮሚቴ ሆነው በጊዜያዊነት በተቋቋመው መጠለያ በመሥራት ላይ የሚገኙት አቶ መለሰ ደሳለው ለተፈናቃዮች ጤና ትኩረት እየተሰጠ አለመሆኑን ነግረውናል። በሚኖሩበት አካባቢ በቂ መጸዳጃ፣ መጠለያ፣ ምግብ እና ውሃ የሌለ በመሆኑ የጤና ችግር እየገጠማቸው እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ከ50 ሰው በላይ በአንድ ድንኳን እንደሚገኝ የገለጹት አቶ መለሰ ይህም ለተላላፊ በሽታዎች እንዳይጋለጡ ስጋት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።
መንግሥት ሁኔታዎች ተለውጠው ወደ ቀዬአቸው እስኪመለሱ ትኩረት በመስጠት አስፈላጊ የህክምና እና የመድኃኒት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

በቻግኒ ከተማ አስተዳደር ያነጋገርናቸው ሐኪም መኮንን ምናየሁ (ዶክተር) ዜጎች ከሚደርስባቸው ግድያ ለመሸሽ ከቀያቸው ሲፈናቀሉ በቅድሚያ ምግብ፣ ውሃ፣ መጠለያ፣ መጸዳጃ እና የህክምና አገልግሎት በፍጥነት ካላገኙ ለተለያዩ የጤና እክሎች ይዳረጋሉ ብለዋል፡፡ ኮሌራ፣ተቅማጥ፣ ወባ፣ ኮሮና ወረርሽኝ፣ የስኳር በሽታ፣ የደም ግፊት፣ ሳንባ ነቀርሳ፣ ድብርት እና ሌሎችም የተፈናቃዮች ስጋት ናቸዉ ብለዋል።
መንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የምግብ፣ የውሃ፣ የመጸዳጃ ቤት እና የጤና አቅርቦት ቅድሚያ ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። ተፈናቃዮች በተጨናነቀ መጠለያ መኖራቸውን የተመለከቱት ዶክተር መኮንን መንግሥት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማቅረብ እና እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ የህክምና ቡድን ማቋቋም እንደሚገባው ተናግረዋል።
የቻግኒ ከተማ አስተዳደር ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ያሬድ ስማቸው ዜጎች ከመተከል ዞን ተፈናቅለው ከመጡበት ቀን ጀምሮ በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች እና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ከጤና መምሪያ፣ ከጤና ቢሮ እና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ ደግሞ የድንገተኛ አደጋ መከላከል እና መቆጣጠር ባለሙያ ተመድቦ ነፍሰጡር፣ የሚያጠቡ እናቶችን እና የምግብ እጥረት ያለባቸውን ሕጻናት የተለየ ድጋፍ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ኀላፊው አስታውቀዋል። ተከታታይ መድኃኒት የሚወስዱ፣ መድኃኒት ጀምረው ያቋረጡ ተፈናቃዮች ለተጨማሪ ህመም እንዳይጋለጡ የወረዳው ጤና ጥበቃ እየሠራ ነው ብለዋል።
ለ927 ተፈናቃዮች እስከ አሁን የህክምና አግልግሎት መስጠታቸውን የተናገሩት አቶ ያሬድ የሆስፒታል እና የጤና ጣቢያ ባለሙያዎች ተናበው እንዲሰሩ መደረጉንም አስረድተዋል።
ከጤና ሚኒስቴር እና ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመሆን ተንቀሳቃሽ ክሊኒክ ተቋቋሞ ተፈናቃዮች ባሉበት ቦታ ሆነው እንዲታከሙ እየተመቻቸ እንደሆነም ነግረውናል፡፡
ከብሔረሰብ አስተዳደሩ አንድ አምቡላንስ ለተፈናቃዮች ብቻ በመመደብ አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ለሚፈልጉት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
ተፈናቃዮች ከሆስፒታል ያላገኙትን መድኃኒት ከጤና ጣቢያ እንዲያገኙ ይደረጋል ያሉት የጤና ጥበቃ ጽሕፈት ኀላፊው በአሁኑ ወቅት በቂ የመድኃኒት አቅርቦት ባለመኖሩ ለተፈናቃይ ታማሚዎች በቂ መድኃኒት ማቅረብ አልተቻለም ብለዋል። የክልሉ ጤና ቢሮም ክትትል የሚያደርጉ ባለሙያዎችን ወደ ሥፍራው እንደተላከ ታውቋል።
ዘጋቢ:- አዳሙ ሽባባው – ከቻግኒ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ