ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ተወላጆች ከ1ሚሊዮን 200 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ፡፡

299
ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ተወላጆች ከ1ሚሊዮን 200 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 21/2013 ዓ.ም (አብመድ)
ከአውስትራሊያ፣ ከአሜሪካ እና ከሌሎች የውጭ ሀገራት የተሰባሰበውን ድጋፍ ወክለው የመጡት ቄስ ጌትነት በቀለ ለጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድጋፉን አስረክበዋል፡፡ በርክክቡ ወቅት ተወካዩ እንዳሉት በሕገወጡ የትህነግ ቡድን ከእርስታቸው ተሰደው በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ተወላጆች ከዘራፊው ቡድን ነጻ በመሆናቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
በተሠራው የሕግ ማስከበር ሥራ ላይ ህይወታቸውን ለሰጡ የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይል እና ሚሊሻ አባላት ድጋፍ ማድረጋቸውን ነው የገለጹት፡፡
ተወካዩ በውጭ የሚኖሩ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት የአማራ ተወላጆች አሁን አካባቢው ሠላማዊ በመሆኑ ከሚያደርጉት ጊዜያዊ ድጋፍ በተጨማሪ በኢንቨስትመንት ለመሳተፍ እና ለማልማት እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
የድጋፍ ገንዘቡን የተረከቡት የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሞላ መልካሙ ከወልቃይት ጠገዴ ጠለምት በዘራፊው ትህነግ ግፍ የተሰደዱ እና በተለያዩ ዓለማት የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች አይዟችሁ በርቱ ለማለት ላበረከቱት ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ተወላጆች ከዚህ በፊትም ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረው ከዕለታዊ ድጋፍ በተጨማሪ በኢንቨስትመንትም ለመሳተፍ እንዲችሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ከተማ አስተዳደሩ እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል፡፡
ተሰደው ከሀገር የወጡት የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ተወላጆች በሀገር ልማት ፕሮጀክቶች ከተማ አስተዳደሩ በለያቸው አምስት የኢንቨስትመንት ቀጣናዎች እንዲሳተፉም ከንቲባ ሞላ መልካሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በውጭ ሀገር የሚኖሩ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ተወላጆች አሁን ካደረጉት ድጋፍ በተጨማሪ ከዚህ በፊት 1 ሚሊዮን 700 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
ዘጋቢ፡- ምስጋናው ብርሃኔ – ከጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየሴቶችን የምርጫ ተሳታፊነት ለማሳደግ መሠራት እንዳለበት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ፡፡
Next article“ኢትዮጵያ የባህላዊ ማዕድን አውጪዎችን እና የማኀበረሰቡን ሕይወት ለማሻሻል የሚያስችሉ የተፈጥሮ ማዕድናትን የያዘች ሀገር ናት” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ