
የሴቶችን የምርጫ ተሳታፊነት ለማሳደግ መሠራት እንዳለበት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 21/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ኀላፊ መስፍን አበጀ እንዳሉት ምርጫ ዲሞክራሲን ተግባራዊ የምናደርግበት አንዱ መንገድ ነው ብለዋል። ፌደራልን እና ክልሎችን ጨምሮ በቀበሌ፣ በወረዳ፣ በዞን እና በብሔረሰብ አስተዳደሮች ሴቶች ተወዳዳሪ ሆነው መቅረብ ቢኖርባቸውም በበቂ ሁኔታ አለመሳተፋቸውን ተናግረዋል።
ሴቶች የመምረጥም ሆነ የመመረጥ ተሳትፎአቸውን ከፍ ለማድረግ እየሰሩ እንደሆነም ገልጸዋል። እንደ አቶ መስፍን መረጃ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በምክር ቤት ደረጃ ሴቶች 35 በመቶ ድርሻ አላቸው፤ በተሰማሩባቸው የሥራ ዘርፎች ውጤታማ ቢሆኑም በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው የተዛባ አመለካከት ተሳትፏቸውን ዝቅ እንዳደረገውም አብራርተዋል፡፡ ይህም ሊስተካከል ይገባል ነው ያሉት ምክትል ኃላፊው፡፡
የማኅበረሰቡን አመለካከት በመቀየር የሴቶችን ተሳትፎ የማሳደግ ተግባር በአንድ ፓርቲ ወይም በመንግሥት ብቻ ሊሠራ የሚችል አለመሆኑንም ጠቁመዋል። መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የመገናኛ ብዙኀኖች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ሊሰሩ እንደሚገባም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ ተናግረዋል፡፡
እንደ ብልጽግና ፓርቲ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ምክትል ኀላፊው አስታውቀዋል፡፡ አቶ መስፍን እንዳሉት የተማሩ ሴቶችን የመመልመል፣ የማደራጀትና የማሰልጠን ሥራ እንደተጀመረ ገልጸዋል። በዚህም የሴቶች ሊግ ትልቁን ድርሻ ይዟል ብለዋል፡፡ “ሴቶችን በአመራርነት ደረጃ ማሳተፍ ቤተሰብንና ሀገርን ማሳተፍ ማለት ነው” የሚለውን መመሪያ ይዘን እየሰራን ነው ብለዋል ምክትል ኀላፊው፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የባሕር ዳር አስተባባሪ መንግሥቱ አማረ በኢትዮጵያ የሴቶች ቁጥር ከወንዶች እንደሚበልጥ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ጠቅሰው በዛ ልክ መሳተፍ እንዳለባቸው ፓርቲያቸው እንደሚያምን ነግረውናል። የማኅበረሰቡ ግማሽ አካል የሆኑት ሴቶች ያልተሳተፉበት ልማት ውጤት ማስመዝገብ አይቻልም ነው ያሉት አስተባባሪው፡፡
ሴቶችን በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ኢዜማ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ “የፖለቲካ ፓርቲዎች ፖሊሲዎቻቸውን ሲያዘጋጁ ሴቶችን ቀጥተኛ ተሳታፊ ማድረግ አለባቸው፤ እኛም ይህን ተግባራዊ እያደረግን ነው” ብለዋል አቶ መንግስቱ፡፡
አቶ መንግስቱ “ካሁን በፊት እንደተለመደው እኛ እናውቅላችኋለን የምንልበት ዘመን ሊያበቃ ይገባል” ብለዋል፡፡
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ (አዴሃን) ሊቀመንበር ተስፋሁን አለምነህ የሴቶችን የመምረጥ እና የመመረጥ መብት ለማረጋገጥ ንቅናቄው እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል። የሴቶችን ተሳትፎ ትኩረት ባለመስጠት ረገድ ባለፉት ምርጫዎች የነበሩ ስህተቶችን መድገም እንደማይገባም ገልጸዋል።
“የኢትዮጵያ ፖለቲካ መስዕዋትነትን የሚጠይቅ በመሆኑ ለሴቶች የተመቸ አልነበረም፤ ለሴቶች የምርጫ ተሳትፎ መዳከም የዲሞክራሲ ግንባታ ዝቅተኛ መሆን፣ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ኀይልን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውና የምርጫ ሂደቱ አግላይ መሆን በዋናነት የሚጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው” ብለዋል ሊቀመንበሩ፡፡
ሴቶች በመምረጥም ሆነ በመመረጥ እንዲሳተፉ ያሉባቸው የገንዘብ፣ የአመለካከትና የተቃራኒ ጾታ ግፊቶች ሊስተካከሉ ይገባል ብለዋል፡፡
ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ያነጋገርናት ወጣት ዜና ዮሐንስ ካሁን በፊት በተካሄዱት ምርጫዎች እንዳልተሳተፈች ገልጻለች፡፡ የባህል ተጽዕኖ፣ የራሳቸው የሴቶች የአመለካከት ችግርና በቤት ውስጥ የሚኖርባቸው የሥራ ጫና በፖለቲካው ሰፊ ተሳትፎ እንዳያደርጉ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተናግራለች፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ገልጻለች፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ