የሲቪክ ማኅበራት፣ የሚዲያ ተቋማትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተግባርና ሚና በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ በሚል ምክክር ተካሄደ፡፡

349
የሲቪክ ማኅበራት፣ የሚዲያ ተቋማትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተግባርና ሚና በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ በሚል ምክክር ተካሄደ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሥሥ 21/2013 ዓ.ም (አብመድ) የቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረስ ፎር ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሕብረት ጋር በመተባበር ነው በአዲስ አበባ የምክክር መድረኩ የተዘጋጀው፡፡
የቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረስ ፎር ዲሞክራሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ታደለ ደርሰህ በዘንድሮው ምርጫ ሕዝቡ ተመራጮችን ብቻ ሳይሆን የፖሊሲ አማራጭ ይፈልጋል ነው ያሉት፡፡
የሲቪክ ማኅበራት እና የመገናኛ ብዙኃን በምርጫ ዙሪያ ከወዲሁ ሕዝቡን በየደረጃው በማስተማርና ግንዛቤ በመፍጠር በኩል ሰፊ ስራዎችን ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። ለመብቱ የሚታገል ለሀገሩ ቀጣይ እጣፈንታ የበኩሉን እንዲወጣ በሚሠራው ሥራ የመገናኛ ብዙኃን ከሲቪክ ማኅበራት ጋር በጋራ ሆነው ሊሰሩ ይገባልም ተብሏል፡፡
ካሁን ቀደም በኢትዮጵያ የተደረጉ ሁሉም ምርጫዎች የነበራቸው አሳታፊነትም ሆነ ዲሞክራሲያዊነት በምሳሌነት የማይጠቀስ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በዚህም የሲቪክ ማኅበራት የተሰጣቸውን ሕዝባዊ ኃላፊነት ሳይወጡ ቀርተዋል ብለዋል፡፡
በዚህ ዓመት በሚደረገው ምርጫ የተፈጠረውን አሳታፊ የዲሞክራሲ ምህዳር በመጠቀም የሲቪክ ማኅበራት ሀገራዊ ምርጫው አሳታፊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌደራሊዝም ምሁር ዶክተር ታየ ብርሀኑ ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሚዲያ ተቋማትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተግባርና ሚና በሚል ጉዳይ ላይ የመነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።
የምርጫ ሂደት ስርዓትን መቀበል ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር ታየ ለዚህ ደግሞ የተዘጋጁ ህጎችና አዋጆችን መቀበልና መፈጸም ያስፈልጋል ብለዋል። የዘንድሮው ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ እንዲሆን የሚዲያ አካላት፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና መንግስት ሚና ከፍተኛ ሊሆን ይገባል ያሉት ዶክተር ታየ ከቅድመና ከድኅረ ምርጫ በኋላ ኃላፊነታቸውንም ሲወጡ የሕዝብን ውሳኔ ባከበረ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።
የመገናኛ ብዙኃን ሚዛናዊ፣ ለሕዝብ እንጅ ለፓርቲ ያልቆሙ ሊሆኑ ይገባል፤ የተሳሳቱ አካሄዶችንም ማረም ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።
የሲቪክ ማኅበራት ለሰላም መጠበቅና ለሀገር መረጋጋት እንዲሰሩም በጽሁፉ ተመላክቷል።
ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያያት እስካሁን የተደረጉ ምርጫዎች ሂደታቸውን ጠብቀው ይከወኑ እንጅ ታማኝነታቸው እና ዲሞክራሲያዊነታቸው ላይ ጥያቄ ውስጥ የወደቀ ነበር ብለዋል፡፡ ይህ በዘንድሮው ምርጫ እንዳይደገም መንግስትም ሆነ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡ በሃገር ውስጥ ያሉ አለመረጋጋቶች እና የፀጥታ ችግር ፈተና ስለሚሆን ከወዲሁ ሥራ ይጠይቃሉ ነው ያሉት።
የፓርቲዎች የተለየ ሚና በዚህ ምርጫ ያስፈልጋል ያሉት ተሳታፊዎች በሂደቱም ሆነ በውጤቱ የሀገርና የህዝብ ደኅንነት እንዲጠበቅ የጋራ ስምምነት ሊኖራቸው እንደሚገባም ተነስቷል።
የማኅበራዊ ሚዲያው በምርጫው ላይ ተፅዕኖ ይዞ እንዳይመጣ ከወዲሁ መስራት ይጠይቃል ተብሏል።
በዓለምአቀፍ መመዘኛ መሰረት ተቀባይነት ያለው ምርጫ ለማድረግ ሁሉም አካል ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተመላክቷል። የሲቪክ ማኅበራት ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የምርጫውን ታማኝነትና ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው የተባለው።
የምርጫ ጊዜው እየደረሰ ቢሆንም ፈቃድ ተሰጥቶን አሁንም ወደ ማስተማርና ግንዛቤ ስራ እንድንገባ ከወዲሁ መመቻቸት አለበት ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ መፈናቀል መረጋጋት በሌላባቸው አካባቢዎች፣ የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች እና አካል ጉዳተኞች በዘንድሮው ምርጫ ላይ በሚሳተፉበት መንገድ ዙሪያ ከወዲሁ ሊሠራ ይገባል ሲሉም ተሳታፊዎቹ አንስተዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች የተነሱ ጉዳዮች በቀጣይ ከሚመለከተው አካል ጋር ውይይት እንደሚካሄድባቸው ይጠበቃል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየደጅአዝማች አያሌዉ ብሩ ቤተመንግሥት ትኩረት ባለመሰጠቱ በዉስጡ የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶችና ግንባታዉ በመፍረስ ላይ መሆኑ ተገለጸ፡፡
Next articleየሴቶችን የምርጫ ተሳታፊነት ለማሳደግ መሠራት እንዳለበት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ፡፡