የደጅአዝማች አያሌዉ ብሩ ቤተመንግሥት ትኩረት ባለመሰጠቱ በዉስጡ የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶችና ግንባታዉ በመፍረስ ላይ መሆኑ ተገለጸ፡፡

506
የደጅአዝማች አያሌዉ ብሩ ቤተመንግሥት ትኩረት ባለመሰጠቱ በዉስጡ የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶችና ግንባታዉ በመፍረስ ላይ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 21/2013 ዓ.ም (አብመድ) የደጅአዝማች አያሌዉ ብሩ ቤተመንግሥት በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ ምዕራብ አቅጣጫ አምስት ኪሎ ሜትር ገባ ብሎ የሚገኝና በጥንታዊ አሠራሩ ከጎንደርና ከጉዛራ ቤተ መንግሥቶች ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነዉ፡፡ ደጅአዝማች አያሌዉ ብሩ ቤተመንግሥታቸዉን የበጌ ምደር ገዥ በነበሩበት ወቅት እንደሠሩት የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
ይህ ቤተመንግሥት በአካባቢዉ ማኅበረሰብ ይታወቅ እንጂ የማስተዋወቅ ሥራ ባለመሠራቱ የቱሪዝም መዳረሻ መሆን እንዳለቻለ ያነጋገርናቸዉ የአካባቢዉ ተወላጆች ገልጸዋል፡፡ ቤተ መንግሥቱ በዉስጡ ደጅአዝማች አያሌዉ ብሩ ይጠቀሙባቸዉ የነበሩ የብራና መጽሐፍቶች፣ አልባሳት፣ የወረቅ ከበሮዎችና ዘዉድ መኖራቸዉን የቤተመንግሥቱ አስጎብኝና የሙዚዬሙ ጠባቂ አቶ ደሳለኝ መራ ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ ይህ ቤተመንግሥት ትኩረት ባለማግኘቱ በመፍረስ ላይ መሆኑን ወጣት አዳነ አደራጀዉና ወይዘሮ እንኳሆነ ጤናዉ ገልጸዋል፡፡ የቤተመንግሥቱ ቅርሶች ካሁን በፊት ከነበራቸዉ ይዘትና ቅርጽ እየወጡ ለብልሽት እየተዳረጉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ቤተመንግሥቱን የጎብኝዎች መዳረሻ ለማድረግ ማስተዋወቅ እንደሚገባ የገለጹት አስተያየት ሰጭዎቹ በተለይ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ለሚገኙ ለአካባቢዉ ተወላጆች በማኅበራዊ ሚዲያና በግል በማስረዳት የድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ቤተመንግሥቱና በዉስጡ የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶች ለትዉልድ እንዲተላለፉ ከወረዳ እስከ ፌደራል የባህልና ቱሪዝም ተቋማት ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡ በደጅአዝማች አያሌዉ ብሩ ቤተመንግሥት ዉስጥ የሚገኙት ጥንታዊ የብራና መጽሐፍቶችና አልባሳት፤ የወርቅ ከበሮዎችና ዘዉዶች በቦታ ጥበት ምክንያት እየተበላሹ እንደሚገኙ የቤተመንግሥቱ አስጎብኝ አቶ ደሳለኝ መራ ገልጸዋል፡፡

ከጥንታዊ ቅርሶች በተጨማሪም ቤተመንግሥቱ ትኩረት ባለመሰጠቱ እየፈረሰ እንደሚገኝና የሚመለከተዉ አካል በቀጣይ ትኩረት በመስጠት ከመፍረስ ሊታደገው ይገባል ብለዋል አቶ ደሳለኝ፡፡የደጅአዝማች አያሌዉ ብሩ ቤተመንግሥትን ለማደስና በዉስጡ የሚገኙ ቅርሶችን ለትዉልድ ለማስተላለፍ የሙዚዬም ግንባታ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ መቀመጡንም ተናግረዋል፡፡

ቤተመንግሥቱን ለማስተዋወቅ የክልሉ መንግሥትም ይሁን የፌደራል መንግሥት ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ የሰሜን ጎንደር ዞን ሀገረ ሰብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኀሩያን እስጢፋኖስ ጥፍጤ አስገንዝበዋል፡፡ ቤተመንግሥቱን የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደስታ ካሳ- ከደባርቅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleለግብርና ምርቶች ጥራት ትኩረት መስጠታቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የምርቱ አቅራቢ ነጋዴዎች ተናገሩ፡፡
Next articleየሲቪክ ማኅበራት፣ የሚዲያ ተቋማትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተግባርና ሚና በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ በሚል ምክክር ተካሄደ፡፡