ለግብርና ምርቶች ጥራት ትኩረት መስጠታቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የምርቱ አቅራቢ ነጋዴዎች ተናገሩ፡፡

242
ለግብርና ምርቶች ጥራት ትኩረት መስጠታቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የምርቱ አቅራቢ ነጋዴዎች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 21/2013 ዓ.ም (አብመድ) የሰሊጥ፣ የአኩሪ አተር፣ የማሾ እና ሌሎች የግብርና ምርቶችን ለጎንደር የኢትዮጵያ ምርት ገበያ (ኢሴክስ) በጅምላ የሚያቀርቡ አካላት ለጥራት ትኩረት መስጠታቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የግብርና ምርት አቅራቢ ነጋዴዎች አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ በፊት የግብርና ምርቶችን አቅም ያለው ነጋዴ በሕገወጥ መንገድ ይሰበስባቸው እንደነበርና ይህም ጥቅም እንዳልነበረው ጠቁመዋል፡፡ ባሁኑ ወቅት ሁሉም ለማዕከሉ ባቀረበው የምርት ጥራት ልክ ደረጃ ተሰጥቶት ዋጋ የሚወጣለት በመሆኑ ተጠቃሚ አድርጎናል ብለዋል የግብርና ምርት አቅራቢ ነጋዴዎቹ፡፡
የደረጃ አሰጣጡ ባመጡት ምርት ጥራት ልክ የወጣ በመሆኑ በአቅራቢዎቹ መካከል ጤነኛ ውድድርን እየፈጠረ ነው፡፡ ኢሴክስ ከምርት መረከብ እና የምርቱን ደረጃ ከማስጠበቅ ባለፈ ሙያዊ እገዛ በማድረግ የሚሰራ በመሆኑ ጥራት ያለው ምርት ወደ ገበያ እንዲመጣ ማድረጉን
ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ (ኢሴክስ) ከመከፈቱ በፊት በሀገር ውስጥም ይሁን ከሀገር ውጭ የሚቀርቡ ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዳልነበሩ አቶ መዝገቡ ክንዴ የምርት ገበያው ጎንደር ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት ጥራት ያለው ምርት ባለመቅረቡ ሀገሪቱ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ እንድታጣ ምክንያት እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በነጋዴዎች መካከል ጤነኛ ውድድር እንዲኖር ለማድረግ ማዕከሉ በሠራው ሥራ አቅራቢዎቹ ምርታቸው ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆንና የተሻለ ገቢ እንዲያስገኝላቸው አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡
ምርት ገበያው ወደታች ወርዶ የምርት ጥራት እንዲጠበቅ በሚሰጠው ሙያዊ እገዛ ከዚህ በፊት በማዕከሉ ይቀርብ የነበረውን የምርት መጠን አሳድጎታልም ነው ያሉት አቶ መዝገቡ፡፡
ማዕከሉ በተያዘው ዓመት 469 ሺህ ኩንታል የሰሊጥ ምርት ለመቀበል አቅዶ በግማሽ ዓመቱ 252 ሺህ ኩንታል ምርት መቀበሉን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ምስጋናው ብርሃኔ-ከጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነቡ ስምንት ትምህርት ቤቶች ለርክክብ ዝግጁ መሆናቸው ተገለጸ።
Next articleየደጅአዝማች አያሌዉ ብሩ ቤተመንግሥት ትኩረት ባለመሰጠቱ በዉስጡ የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶችና ግንባታዉ በመፍረስ ላይ መሆኑ ተገለጸ፡፡