“በትግራይ ክልል በነበረው ሕግ የማስከበር ተግባር ሴቶች ቆራጥነታቸውንና ጀግንነታቸውን በተግበር አሳተዋል” የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ወርቅሰሙ ማሞ

277
“በትግራይ ክልል በነበረው ሕግ የማስከበር ተግባር ሴቶች ቆራጥነታቸውንና ጀግንነታቸውን በተግበር አሳተዋል” የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ወርቅሰሙ ማሞ
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 20/2013 ዓ.ም (አብመድ) በሥርዓተ-ፆታ እኩልነትና ሴቶችን በማብቃት ላይ የሚሠራው እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል የሆነው (ዩኤን ውሜን) ጋር በመተባበር በመጪው ሀገራዊ ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ ውይይት በባሕር ዳር ተካሂዷል፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ወርቅሰሙ ማሞ “ስለ ሴቶች የምርጫ ተሳትፎ ስናወራ ለሴቶች ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ለሀገሪቱ ካለው ፋይዳ አንፃር መታየት አለበት” ብለዋል በውይይቱ የመክፈቻ ንግግራቸው፡፡ ሴቶች በሁሉም መስክ ተሳታፊነታቸውን ከፍ በማድረግ ባላቸው ብቃት ሀገርን የመቀየር ሚና እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡
እንደ አፈ ጉባኤዋ ገለጻ በትግራይ ክልል በነበረው ሕግ የማስከበር ተግባር ላይ የነበሩ ሴቶች ቆራጥነትንና አልሸነፍ ባይነትን በተግበር አሳተዋል፤ ሴቶች ከሕግ ማስከበሩ በተጨማሪ በልማቱም እያደረጉት ያለው ተሳትፎ ከራስ አልፎ ለሌሎች የመሆንን ሚስጥር እያሳየ ነው፡፡
በተለይ ደግሞ ሴቶችና ሠላም የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የአማራ ክልል ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ወይዘሮ አስናቁ ድረስ ከአሁን በፊት የነበሩ ምርጫዎች ላይ የሴቶች ተሳትፎ አናሳ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አሁንም ከሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ በርካታ ተግባራት መከናወን አለባቸው ብለዋል፡፡
በአስፈጻሚነት ቦታ ያለው አካል ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል ተሳትፎ ይኖራቸዋል ብሎ አለማመንም በዋናነት የሚታይ ችግር እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ አቅም ያላቸው ሴቶች እንዲኖሩ በመሥራት በኩልና በሚመጥን ቦታ በማስቀመጥ በኩልና እድሉን አግኝተው ቦታ ከያዙ ደግሞ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ በማድረግ በኩል ውስንነቶች እንዳሉ ኀላፊዋ ገልጸዋል፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ በማኅበረሰቡ፣ በሴቶቸና በሥራ ኀላፊዎች ጠንካራ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ በዩኤን ውሜን ኢትዮጵያ ሴቶችን ወደ አመራርነት የማምጣትና የፖለቲካ ተሳታፊነታቸውን የማሳደግ ፕሮግራም ኀላፊ ደሴት አበበ ከሁን በፊት በነበረው ምርጫ የሴቶች ድርሻ በምክር ቤት 38 በመቶ በክልል 47 በመቶ መድረሱን ጠቅሰዋል፡፡ ወደ ዞኖችና ወደ ወረዳ ግን ከ30 በመቶ በታች መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ይህን ችግር ለመቅረፍ መሠራት አለበት ብለዋል፡፡ እስካሁንም አጫጭር ስልጠናዎች ሲሰጡ መቆየታቸውን እና በቀጣይ ዘላቂነት ባለው መንገድ ለማስቀጠል እየሰሩ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ሴቶች በቀጣዩ ምርጫ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቀርቡ ጥረት እንደሚደረግም ኀላፊዋ ተናግረዋል፡፡
ከተመረጡ በኋላ የአካባቢው ተጽእኖ ወደ ኋላ እንዳይጎትታቸው የለውጥ አመራር ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ “የሴቶችን የአመራር እና የፖለቲካ ተሳትፎ በመጪው ምርጫ ማሻሻል” በሚል መሪ ሀሳብ ክልላዊ ውይይቱ ተካሂዷል። በውይይቱ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሚዲያ ተቋማት ፣ የምክር ቤት አመራሮች አና ሌሎች አካላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡-ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 5ኛ 5 ዓመት 6ኛ የሥራ ዘመን 6ኛ አስቸኳይ ጉባዔ የ4 የምክር ቤት አባላትን ያለመከሰስ መብት አንስቷል፡፡
Next articleበቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነቡ ስምንት ትምህርት ቤቶች ለርክክብ ዝግጁ መሆናቸው ተገለጸ።