
“መከላከያ ሠራዊትና የአማራ ልዩ ኀይል አካባቢውን ሲቆጣጠር ደስታዬ ወደር አልነበረውም፣ ምክንያቱም ያሳለፍኩት ፈተና ከባድ ነው” አልማዝ አብርሃ የዛዲግ አብረሃ ታላቅ እህት
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 20/2013 ዓ.ም (አብመድ) አድርግ የተባልከውን ታደርጋለህ፣ ለምን ብሎ መጠየቅ በዚያ ዘመን የተከለከለ ነው። አድርግ የተባልከውን ካላደረክ ትገረፋለህ፣ ትታሰራለህ፣ ትሰቃያለህ ትገደላለህም። የእናት እንባ አያራራቸውም፣ በዚያ ዘመን እናት አልቅሳለች፣ በናፍቆት ተጎድታለች፣ ባልወለደኩ ስትል ተመኝታለች።
የኢትዮጵያውያን እናት ካለቀሰች ከዙፋን ታወርዳለች፣ የበረታን ታደክማለች፣ ግፈኛን ታስቀጣለች፣ ኢትዮጵያዊት እናት እንባዋ ለግፈኞች ሩቅ ቢሆንም ለፈጣሪዋ ግን ቅርብ ነው። ይሰማታል፣ ፈጥኖም ይፈፅምላታል። ስለሀገር ታለቅሳለች፣ ስለሰላም ፈጣሪዋን ትለምናለች። ስለ ልጆቿ መልካሙን ሁሉ ትመኛለች። ደግሞ ግፉ ከፍ ሲል አንባዋን ቆጥባ ነፍጥ አንስታ ትዋጋለች።
ኢትዮጵያዊት እናት ፀሎተኛ ብቻ ሳትሆን አርበኛም መሆን ታውቅበታለች። ዘላለማዊ ባልሆነ ምድራዊ ዙፋን፣ የዘላለምን መንገድ የሚዘጋ ክፉ ሥራ መሥራት ከፈጣሪም ከሰውም ጋር ያራርቃል። “ሰው ፈርዶ ለእግዚአብሔር” እንዲሉ እማሆይ የሰው የልብ ሀዘንና ልመና ከፈጣሪ ይደርሳል። በውሸት የተሸፈነ ጀግንነት፣ እኔ ብቻ ልቅደም የሚል ኢትዮጵያዊነት እድሜው አጭር ነው።
ኢትዮጵያዊነት እውነት፣ ኢትዮጵያዊነት ትዕግሥት፣ ኢትዮጵያዊነት ብልኀት፣ ኢትዮጵያዊነት አርቆ አሳቢነት፣ ለሰው ሲሉ ኗሪነት፣ ኢትዮጵያዊነት ሚስጥር፣ ኢትዮጵያዊነት ክብር፣ ኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ ኢትዮጵያዊነት አብሮነት ነው።
ዘረኝነትን፣ ራስ ወዳድነትን፣ መለያዬትን እየሰበኩ ኢትዮጵያዊነትን መኖር አይቻልም፣ ኢትዮጵያዊነት ከምንም በላይ ነው። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንን ክዷቸዋል ይሉታል፣ ወንድም ወንድሙን እንዲጠራጠር፣ ሰው አምኖ ሚስጥር እንዳይነግር አድርጎ ቆይቷል። ከባልንጀራ ጋር ተሰባስቦ መጨዋወት አሸባሪ፣ ፀብ ቀስቃሽ ያስብል ነበር- በዘመነ ትህነግ።
በትህነግ ግፍ ልባቸው ሲያዝን፣ የእናት እንባቸው ሲፈስ ከነበሩ እናት ጋር ቆይታ አድርገናል። ወይዘሮ አልማዝ አብረሃ ይባላሉ። በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል የዘርፍ አስተባባሪ ዛዲግ አብርሃ ታላቅ እህት ናቸው። ነዋሪነታቸው በራያ አላማጣ ነው። ወይዘሮ አልማዝ ትህነግ ሕይወታቸውን ከፈተነውና ካመሰው የራያ እናቶች መካከል አንደኛዋ ናቸው። ትህነግ አካባቢውን ለቅቆ እስኪወጣ ድረስ ከባለቤታቸውና ከልጃቸው ጋር ተለያይተው እንዲኖሩ ፈርዶባቸው ነበር።
የእብሪተኛነቱ ልክ ተፈታትኗቸዋል። ጠንካራ ነበሩና ሳይሰበሩ ግፉን ተቋቁመው አዲስ ቀን አይተዋል። “በትህነግ ዘመን ነገ ምን ይመጣብኝ ይሆን? ነገ ደግሞ ምን እባላለሁ? በማለት በሰቀቀን ነበር የምኖረው። በሰቀቀን ውስጥ ስኖር የነበርኩ ሰው ነኝ፣ የራያ ሕዝብም በስቃይና በሰቀቀን ሲኖር ነበር” ብለዋል። በተለይ በኢትዮጵያ ለውጥ ከመጣና ወጣቶች ለማንነታቸው መከበር ሰልፍ ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ የነበረው ስቃይ የከፋ እንደነበር ነው የተናገሩት።
ወይዘሮ አልማዝ በተደጋጋሚ ሲታሰሩና ሲንገላቱ ቆይተዋል። በነበረው እንግልት ባለቤታቸውና ልጃቸው ከአላማጣ ወጥተው በቆቦ እንዲኖሩ ተገደዋል። “ቆቦ ሄደሽ ነበር ነይ እስር ቤት ግቢ፣ ቆቦ ሄደሽ ለባለቤትሽና ለልጅሽ ስንቅ አቀብለሻል ነይ ታሰሪ፣ እስከ መቸውም የማረሳው ሕዝብ መሀል ቆሜ ሕዝብን ይቅርታ ጠይቂ የተባልኩበት ነው። ምን አደረኩና ነው ይቅርታ የምጠይቀው? እድል ስጡኝ ከሕዝቤ ጋር ልነጋገር፣ ሕዝቡ የሚለኝን ሰምቼ ይቅርታ ልጠይቅ አልኩ፣ እድል የሚባል ነገር የለም፣ ወደድሽም ጠላሽም ይቅርታ ትጠይቂያለሽ፣ ካለበለዚያ ትታሰሪያለሽ ተባልኩ። አሰሩኝ፣ ከእኔ ግን ያገኙት ለውጥ የለም።
ባለቤቴም ልጄም በስደት ቢሆኑም አልተሸበርኩላቸውም። በአንገቴ ቀርቶ በጀርባዬ እረዱኝ ነው ያልኳቸው” ነው ያሉት ያን ዘመን ሲያስታውሱ።
ትህነግ በግፉ እሳቸውም በማይናወጥ አቋማቸው ቀጠሉ። የባለጊዜዎች ዘመንም አልፎ ሌላ ዘመን መጣ። ማነው ወንዱ ሲሉ የነበሩት ፈርጥተው ጠፉ። ለዓመታት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ፈርደውበት የነበረውን መሳደድ እነሱም ተቀበሉት። አሁን ጊዜው አልፎ ከልጃቸውና ከባለቤታቸው ጋር ተገናኝተዋል። ደስታቸውንም እያጣጣሙ ነው። አካባቢውን መከላከያ ሠራዊት የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ከትህነግ ነፃ ሲያወጣው ደስታቸው ላቅ ያለ እንደነበርም ነግረውናል።
“መከላከያ ሠራዊትና የአማራ ልዩ ኀይል አካባቢውን ሲቆጣጠር ደስታዬ ወደር አልነበረውም፣ ምክንያቱም ያሳለፍኩት ፈተና ከባድ ነው፤ ብዙ መከራ የደረሰባቸው ሰዎች አሉ። እኔም ከሰው ተገልዬ እንድቆይ ተደርጌአለው፤ ብዙ መከራ አሳልፊያለው። ሌላው ቀርቶ ለሬሳ መቀበሪያ እንኳን እድር ድረስ መጥተውብኛል፤ ከእድር አስወጥተውኛል። ሠራዊቱ በመግባቱ ሀገር ሰላም በመሆኗ፣ ከሕዝብ ጋር በደስታና በሰላም በመገናኜቴ በጣም ደስተኛ ነኝ በጣምም እኮራለሁ” ነው ያሉት። ታናሽ ወንድማቸው አቶ ዛዲግ አብርሃ ከትህነግ ወጥተው መታገል ከጀመሩ ወዲህ ደግሞ የባሰ ግፍ ሲደርስባቸው እንደነበርም አስታውሰዋል። “ዛዲግ የትህነግን አካሄድ በመቃወም ከወጣ በኋላ፤ እርሱ ባንዳ ነው፣ አንቺ የእርሱ ተከታይ ነሽ፣ ሰላይ ነሽ፣ እኛ አማራ ነን ትያለሽ፣ ከእርሱ መልዕክት ትቀበያለሽ የሚል ማሸማቀቅ ይደርስብኝ ነበር” ብለውናል። በነበረው ጫና ቤታቸው በየጊዜው ይፈተሽ እንደነበርም ነግረውናል።
“አሁን ግን ለውጥ አይተናል ወንደሜንም ደስ ይበለው እኔንም ደስ ብሎኛል” ነው ያሉት። ያ ሁሉ ጫና ሲመጣ ባለቤታቸውን እና ልጃቸውን አይዟችሁ ከጎናችሁ ነኝ፣ ወደ ኋላ እንዳትመለሱ ከማለት በስተቀር እኔ ላይ ጉዳት ይደርስብኛል ብዬ አልፈራኋቸውም ነው ያሉን። የራያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የራያ መሬት ብዙ ግፍ ደርሶበታል ያሉት ወይዘሮ አልማዝ ራያ እንዳትለማ መደረጉንም ተናግረዋል። እሳቸው ሲሰቃዩ አይዞሽ ሲሏቸው የነበሩትን ሁሉ ከደስታ ማግስት አመስግነዋል። አባት ተመልሶ፣ እናትና ልጅ ተገናኝተው የቤቱ ደስታ ተመልሷል።
የአላማጣ ጎዳናዎች ናፍቀዋቸው የነበሩ ወጣቶች በነፃነት መጓዝ ጀምረዋል። ያለ ጥርጣሬ ማውጋት፣ ያለ ስጋት መጫዎት ተጀምሯል።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ