
የአፍሪካ አህጉር አቋራጭ የፍጥነት መንገድ አካል የሆነውና በቅርቡ የተመረቀው የኢትዮ- ኬንያ መንገድ የኢትዮጵያን የወደብ አማራጭ የሚያሰፋ መሆኑ ተገለፀ።
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 20/2013 ዓ.ም (አብመድ) በኢትዮጵያ በኩል ከሀዋሳ ሞያሌ 500 ኪሎ ሜትር እና በኬንያ በኩል ደግሞ ከኢሲኦሎ እስከ ሞያሌ የ503 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ ተጠናቆ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ እና በኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ መመረቁ ይታወሳል።
የአፍሪካ አህጉር አቋራጭ የፍጥነት መንገድ አካል የሆነው መንገድ አዲስ አበባን ከካይሮ፣ ጋቦሮኒ፣ ኬፕ ታውን እና ኬንያ-ሞምባሳ የሚያገናኝ ከመሆኑም ባሻገር ደቡብ ሱዳንን-ከኬንያ ላሙ ወደብ ጋር ለማገናኘት የሚያስችል ነው።
በብሔራዊ ሎጅስቲክ ምክር ቤት የሎጅስቲክ ትራንስፎስሜሽን ጽሕፈት ቤት የሎጅስቲክ ባለሙያው አቶ ተመስገን ይሁኔ እንዳሉት መንገዱ ለንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ትስስር ካለው ጠቀሜታ ባሻገር በወደብ ተጠቃሚነት የኢትዮጵያን የመደራደር አቅም የሚያሳድግ ነው።
ግንባታው ሲጠናቀቅ በአንድ ጊዜ 32 መርከቦችን ማስተናገድ የሚችለውን የላሙ ወደብ ለመጠቀም መንገዱ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል።
ወደቡ በተለይ ለደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ የወጪና ገቢ ንግድን ለማሳለጥም ከፍ ያለ ፋይዳ እንዳለው አስገንዝበዋል። በተለይም የኢንዱስትሪ መንደር ለሆኑት ሀዋሳ፣ ይርጋዓለምና ያቤሎ አካባቢዎች ጥሩ አማራጭ በመሆን ጊዜና ገንዘብ ይቀንሳል ብለዋል።
የመንገዱ መገንባት ከትራንስፖርትና ወደብ ታሪፍ አንጻር አማራጭ በመሆን የኢትዮጵያን የወደብ መደራደር አቅም እንደሚያሳድግም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር ያላትን የንግድ ትስስር ከማሳደግ በተጨማሪ ምርቶቿን ወደ ለዓለም ገበያ የማቅረቢያ ዋና ኮሪደር ሆኖ ያገለግላልም ብለዋል።
የመንገዱ መገንባት 3 ቀናትና ከዚያ በላይ ይፈጅ የነበረውን የየብስ ትራንስፖርት ጉዞ ወደ 10 እና 8 ሰዓት ዝቅ አድርጎታል ነው ያሉት።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደተናገሩት ኢትዮጵያና ኬንያ በሰላም ማስከበርና በፖለቲካ ዘርፍ ያላቸውን ጠንካራ ግንኙነት በምጣኔ ሃብትም የማጠናከር ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። በመሆኑም የኢትዮ-ኬንያ መንገድ በተለይ የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ንግድ ለማሳለጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለው አንስተዋል።
ከሐዋሳ-ሞያሌ የሚዘልቀው 500 ኪሎ ሜትር መንገድ እና የጋራ ፍተሻ ኬላ የጉምሩክ፣ የኢሚግሬሽን፣ የጤና እና የደረጃ ድርብርብ ፍተሻ የሚያስቀር መሆኑንም ገልጸዋል። በዚህም የጉምሩክ ሥርዓቱን ግልጽ፣ ቀላል እና ቀልጣፋ ያደርገዋል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አፍሪካን ለማስተሳሰር በሕብረቱ በእቅድ የተያዘው የትራንስ አፍሪካ አውራ ጎዳና መንገድ አካል የሆነው ይህ መንገድ ሌሎች የአፍሪካ አገራትንም የሚያስተሳስር ይሆናል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ