“የፎገራ የሩዝ ምርትን እሴት ጨምሮ ለመሸጥ የሚያስችል ማሽን በግዢ ሂደት ላይ ነው” የወረዳዉ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጽሕፈት ቤት

406
“የፎገራ የሩዝ ምርትን እሴት ጨምሮ ለመሸጥ የሚያስችል ማሽን በግዢ ሂደት ላይ ነው” የወረዳዉ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጽሕፈት ቤት
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 20/2013 ዓ.ም (አብመድ) የፎገራ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት በዘንድሮ የምርት ዘመን ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሩዝ ምርት ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።
አርሶ አደር አግማስ ሙጨ በፎግራ ወረዳ የቋር ጊዮርጊስ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ለወራት የደከሙበትን የሩዝ ምርት ወደ ቤታቸው ለማስገባት በከብቶቻቸው ሲወቁ ነበር ያገኘናቸው። ይሁን እንጂ የገበያ ትስስር ባለመኖሩ የሩዝ ዋጋ ከባለፈዉ ዓመት መቀነሱን ተናግረዋል። በኪሎ ግራም ከ 15 ብር ወደ 10 ብር ወርዷል ብለዋል።
ሩዝን በመስመር እንደሚዘሩ የተናገሩት አርሶ አደሩ ከአንድ ጥማድ እስከ 25 ኩንታል ምርት አግኝተዋል። ወረዳዉ ምርጥ ዘር ቢያቀርብላቸውም የተሻለ የገበያ አማራጭ በመፍጠር ግን ችግር እንዳለ ተናግረዋል።
በፎገራ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ዓለሙ ሙሉቀን በወረዳዉ 57 ሺህ ሄክታር በተለያዩ ሰብሎች እንደተሸፈነ ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥ ከ22 ሺህ ሄክታር በላይ ደግሞ በሩዝ የተሸፈነ ነው ብለዋል። በምርት ዘመኑ ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ የሆኑ የሩዝ አምራች ቀበሌዎች ድረስ በመገኘት በተሠራው የምርት ቅድመ ግምገማ መሠረት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ባለሙያው አብራርተዋል።
በ2012 ዓ.ም በወረዳዉ በተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ ስድስት ቀበሌዎች ጉዳት እንዳደረሰባቸው ያስታወሱት ባለሙያዉ በዚህ ምክንያት ወረዳዉ ማግኘት ከሚገባው የሩዝ ምርት 1 መቶ 19 ሺህ ኩንታል ሊያጣ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ጽሕፈት ቤታቸዉ አርሶ አደሮች በኩታ ገጠምና አስፈላጊዉን ግብዓት እንዲጠቀሙ በማድረግ የተሻለ ምርት እንዲያገኙ ማስቻሉን ተናግረዋል። የሩዝ ምርት በወረዳቸው አዲስ እንደመሆኑ መጠን አርሶ አደሮቹ በማኅበራት ተደራጅተው በሚፈለገው መልኩ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉም አስረድተዋል።
የፎገራ ወረዳ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ጌትነት አስፋው በፊት በወረዳዉ ሩዝ ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ ማኅበራት የሩዝ መፈልፈያ ማሽን እንዳልነበራቸው ጠቅሰው በ2013 ዓ.ም ግን ከዘጠኝ ማኅበራት ስምንቱ የመፈልፈያ ማሽን በመግዛት እሴትን ጨምረው እየሸጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
አርሶ አደሮቹ የለመዱት የሩዝ ምርታቸዉን አስፈልፍለው መሸጥ እንደሆነ የተናገሩት ኀላፊዉ ይህ አሠራር ስለሚጎዳቸው ምርታቸዉን ከነ ገለባው ለማኅበራት ቢያስረክቡ የተሻለ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ብለዋል።
ፎገራ ወረዳ ካለው ከፍተኛ የሩዝ ማምረት አቅም ጋር ሲታይ ያሉት የኅብረት ሥራ ማኅበራት በቂ እንዳልሆኑ ያስረዱት ኀላፊው ቁሀር ኀላፊነቱ የተወሰነ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበርና ከአግሮ ቢግ ጋር በመተባበር የሩዝ ምርትን አቀነባብሮ ወደ ውጭ የሚላክበተ ስልትን ቀይሰው እየሠሩ እንደሆነ ጠቁመዋል።
አርሶ አደሮችም ሆነ ወረዳዉ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከጊዜ ወደጊዜ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያስረዱት ኀላፊው “የወረዳዉን የሩዝ ምርት እሴት ጨምሮ ለመሸጥ ያስችላል ተብሎ የሚገመት እንዲሁም ከውጭ የሚገባ ሩዝን ማስቀረት የሚችል ማሽን በግዢ ሂደት ላይ ይገኛል” ብለዋል።
ዘጋቢ:- ብሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበኩር ጋዜጣ ታህሳስ 19/2013 ዓ/ም ዕትም
Next articleየአፍሪካ አህጉር አቋራጭ የፍጥነት መንገድ አካል የሆነውና በቅርቡ የተመረቀው የኢትዮ- ኬንያ መንገድ የኢትዮጵያን የወደብ አማራጭ የሚያሰፋ መሆኑ ተገለፀ።