
በመተከል ዞን በተደጋጋሚ የደረሰው ሞት፣መፈናቀል እና የንብረት መውደም ለሀገሪቱ ትልቅ ስጋት መሆኑን መንግሥት ሊረዳው እንደሚገባ ተፈናቃዮች ተናገሩ።
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 19/2013 ዓ.ም (አብመድ) በመተከል ዞን ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች በደረሠባቸው ሞት እና የንብረት መውደም ለችግር መጋለጣቸውን ለአብመድ ተናግረዋል።
ወጣት እሱባለው ካሱ “በመተከል ዞን ለሀገር አንድነት ደንታ የሌላቸው አረመኔዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ ፈጽመዋል” ብሏል።
ጭፍጨፋውን የፈጸሙት አረመኔዎች በተውሰኑ የክልሉ አመራሮች እየተደገፉ መሆኑን የተናገረው ወጣት እሱባለው አማራውን ሆንብሎ የማሳደድ ሥራ ከዓመታት በፊት መጀመሩን ተናግሯል። ሌላው በጥቃቱ ሶስት ልጆቹንና ባለቤቱን በሞት ያጣው አቶ አለሙ በየነ የታጠቁ ኀይሎች ንጹሃን የአማራ ተወላጆችን ለማሳደድ ዘመናዊ ስልጠና ሲወስዱ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
የችግሩን አሳሳቢነት ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ጥቆማ ቢሰጡም የሚሰማ አካል እንዳላገኙ ገልጸውልናል። በአሁኑ ወቅት በመተከል ዞን እየደረሰ ያለው ጅምላ ጭፍጨፋ በዚህ ከቀጠለ የሀገር ህልውና አደጋ ላይ እንደሚወድቅ አስረድተዋል።
“አሁንም በየቀኑ ተጨማሪ አስክሬን እየተገኘ ነው” የሚሉት አቶ ዓለሙ መንግሥት ፈጣን ርምጃ ወሥዶ ቀሪ ወገኖችን እንዲታደግና አካባቢው ተረጋግቶ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ጠይቀዋል፡፡
ሌላዋ ተፈናቃይ ትግሥት ተስፋየ “የአማራ ተወላጆች ተለይተው ከቤታቸውና ከእርሻ ቦታቸው እየተገደሉ ነው፤ በመተከል ዞን በተደጋጋሚ የሚደርሰው ሞት እና መፈናቀል ዘርን መሰረት ያደረገ ነው” ብላለች፡፡
ጭፍጨፋው አሳዛኝና ጭካኔ የተሞላበት መሆኑን ነው የተናገረችው፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጭፍጨፋውን ሊቃወመው ይገባል ብላለች።
ዘጋቢ:-አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ