
በመተከል ዞን የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል እንዲቋቋም ውሳኔ መተላለፉን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 18/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአስቸኳይ ጊዜ አስተባባሪ ማዕከል ዘርፈ ብዙ ምላሽ ሰጪ ብሔራዊ ግብረ ኀይል በሃገሪቱ በተከሰቱ ሰብዓዊና ማኅበራዊ ቀውሶች ፈጣን ምላሽ አሰጣጥ ተግባራትን ለመገምገም መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።
ግብረ ኀይሉ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በተፈጸመው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የዕለት ደራሽ ሰብዓዊ እርዳታ የማዳረስ ተግባራትን በተመለከተ እንዲሁም በትግራይ ክልል እና አጎራባች የአማራና አፋር ክልሎች ትህነግ በከፈተው ጦርነት ምክንያት የተጎዱ አካባቢዎችን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ እና ዜጎችን በዘላቂነት የመልሶ የማቋቋም ተግባራትን ሂደት ገምግሟል።
በብሄራዊ አደጋ ስጋት አስተዳደር ኮሚሽን አስተባባሪነት በመተከል ዞን በቅርቡ በተመሰረቱት ካምፖች ለሚገኙ ወገኖች የዕለት ደራሽ እርዳታ ማከፋፈሉ ቀጥሏል፤ የዕለት ደራሽ እርዳታ የያዙ የጭነት መኪኖች ወደቦታው መንቀሳቀሳቸው ተገልጿል፡፡
በሰላም ሚኒስቴር የሚመራው የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞን፣ እና ሌሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጭ አካላትን የያዙ ቡድኖች በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን፣ በአማራ፣ በአፋር እንዲሁም በትግራይ የሚገኙ ሲሆን በቡድኖቹ የተጠናቀሩ የየዕለት ተግባራት ሪፖርቶችና የኮሚቴው አባላት አመራሮች በቦታው ተገኝተው ባደረጓቸው የመስክ ምልከታ ላይ ተመስርቶ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ገምግሞ ቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጧል።
ግብረ ኀይሉ በመተከል ዞን የአስቸኳይ ጊዜ ተግባራት ማስተባበሪያ ማዕከል (Emergency Operations Center) እንዲቋቋም ውሳኔ አስተላልፏል። በዚህም በሰላም ሚኒስቴር ሚኒስቴር ዴኤታዎች የሚመራ የአመራሮችና ባለሙያዎች ግብረ ኀይል በቦታው ተገኝቶ ለማስተባበር እንዲሁም እንደየአስፈላጊነቱ አመራርና ውሳኔ ለመስጠት ወደ መተከል ዞን መጓዙን የሰላም ሚኒስቴር በማኅበራዊ የትስስር ገጹ አመላክቷል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ