የሀገር መከላከያ ሠራዊት ትህነግን በማስወገድ ያስመዘገበውን ድል በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩትን ግድያዎች በማስቆም ሊደግም እንደሚገባ የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 18/2013 ዓ.ም (አብመድ) ህገ ወጡ የትህነግ ቡድን በሃገር መከላከያ ሰራዊት ላይ በፈፀመው አስነዋሪ ድርጊት የኢትዮጵያውያንን ስሜት ክፉኛ ጎድቶ ነበር፡፡ ህግ በማስከበሩ ርምጃም በአራቱም ጫፍ የሚገኘው የኢትዮጵያ ህዝብ ከመከላከያ ጎን መቆሙን ሲገልፅ ቆይቷል፡፡ ጥቃቱ በተፈፀመባቸው የትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚገኙ ህዝቦች ደግሞ መከላከያ ኀይሉ ከተሰነዘረበት ጥቃት አገግሞ ለድል እንዲበቃ ታሪክ በዘመን መካከል የማይሽረው አኩሪ ገድል ፈፅመዋል፡፡
ትህነግ በሰነዘረው ጥቃት ቀጥተኛ ዒላማ መከላከያ ሰራዊት እና የአማራ ህዝቦች በመሆናቸው ይህንን ጥቃት ከመከላከል አልፎ በተለያየ የጉዳት ደረጃ ላይ የነበሩ የመከላከያ እና የፌደራል ፖሊስ አባላትን ተቀብሎ አስተናግዷል፡፡ በህገ ወጡ ቡድን አፈና ደርሶባቸው ለሳምንታት በርሃብ፣ በውሃጥም እና ድካም በህይዎት እና ሞት መካከል የነበሩት የመከላከያ አባላት በበየዳ እና ጠለምት ወረዳዎች በኩል አድርገው ወደ ስሜን ጎንደር ዞን አካባቢዎች ሲገቡ ህዝቡ በፍቅር ተቀብሎ አስተናግዷቸዋል፡፡
የአማራ ህዝብ ለሰራዊቱ ላደረገው እንክብካቤ፣ ፍቅር እና ድጋፍ በሃገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ጎንደር እና ምዕራብ ጎንደር ዞን ኮማንድ ፖስት የምስጋና እና እውቅና መርሃ ግብር ትናንት በደባርቅ ከተማ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በምስጋና መርሃ ግብሩ የተገኙት የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎችም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ትህነግን በማያዳግም መልኩ በማስወገድ ያሳየውን አኩሪ ጀብዱ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚፈጠሩ የሰላም መደፍረስ ችግሮችን እንዲያስቆም ጠይቀዋል፡፡
‹‹የትናንቱ ድል የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ድል ነው›› ያሉት የደባርቅ ከተማ ነዋሪ አቶ መኳንንት ደሳለኝ ጦርነቱ ቢያልቅም ዛሬም የተልዕኮ ፈፃሚዎች ሴራ ፈፅሞ አልከሰመም ብለዋል፡፡ በመተከል እና በሌሎች አካባቢዎች ያለውን ግድያና መፈናቀል ማስቆም የሰራዊቱን ተልዕኮ የሚሻ በመሆኑ የትናንቱን ገድላችሁን በመፈፀም ኢትዮጵያን መታደግ ይኖርባችኋል ነው ያሉት አቶ መኳንንት፡፡
ሰራዊቱ ከልጆቻችን መካከል እንደ አንዱ ነው ያሉት ሌላዋ የደባርቅ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ እናንየ መስፍን ከደረሰበት የስነ ልቦና ስብራት አገግሞ እና ተልዕኮን በብቃት ፈፅሞ በዚህ መልኩ ለምስጋና መገኘታችን አስደሳች ነው ብለዋል፡፡ የስሜን ህዝብ ያሳየው ፍቅር፣ እንክብካቤ እና ጀግንነትም አማራ ጠላቶቹ እንደሚሉት ሳይሆን ለኢትዮጵያ አንድነት ያለውን ጥልቅ ፍቅር ዳግም ያስመሰከረ በመሆኑ ኮርተንበታል ብለዋል፡፡
በዕለቱ ለምስጋና የተገኙት የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላትም ህዝቡ በህግ ማስከበር ርምጃው ያደረገውን ገድል ታሪክ እና የመከላከያ ኀይሉ ዘላለም ሲዘክረው እንደሚኖር ገልፀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – ከደባርቅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleዘጠኝ መቶ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት የተያዘላቸው የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች የውል ስምምነት ተፈረመ፡፡
Next articleበመተከል ዞን የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል እንዲቋቋም ውሳኔ መተላለፉን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡