ዘጠኝ መቶ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት የተያዘላቸው የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች የውል ስምምነት ተፈረመ፡፡

209
ዘጠኝ መቶ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት የተያዘላቸው የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች የውል ስምምነት ተፈረመ፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 17/2013 ዓ.ም (አብመድ)
የአማራ ክልል ውኃ መስኖና ኢነርጅ ልማት ቢሮ በመካነ ሰላም ከተማ አስተዳደር የሚገነባውን የተቀናጀ የመስኖና የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት እንዲሁም በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አሥር ቀበሌዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ግንባታን ለማሠራት ከአማራ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ጋር ተፈራርሟል፡፡
የአማራ ክልል ውኃ መስኖና ኢነርጅ ልማት ቢሮ ኀላፊ ዶክተር ማማሩ አያሌው የፕሮጀክቱ ግንባታ በአማራ ክልል በዋግኽምራና በደቡብ ወሎ ዞን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግርን እንደሚቀንስ ተናግረዋል፡፡
በዋግኸመራ የሚገነባው የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት 488 ሚሊዮን ብር ተመድቦለታል፡፡ የበጀት ምንጩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ነው፡፡ ግንባታው በአንድ ዓመት ተጠናቆ አገልግሎት ይሰጣል፤ ከ17ሺህ በላይ ሰዎችንም ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል ዶክተር ማማሩ፡፡
በደቡብ ወሎ ዞን በመካነ ሰላም ከተማ አስተዳደር የሚገነባው የተቀናጀ መስኖና የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት በሦስት ዓመት ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡
የገፀ ምድር ውኃን ተጠቅሞ የሚገነባው ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ከ80 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል፤ ከክልሉ መንግስት በተመደበ 410 ሚሊዮን ብር ግንባታው ይካሄዳል ነው ያሉት ዶክተር ማማሩ፡፡
የውል ስምምነቱን የፈረሙት የአማራ ውኃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘመነ ፀሐይ ግንባታውን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ሠርቶ ለማጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርገናል ነው ያሉት፡፡ ድርጅቱ የሕዝቡን በውኃ የመልማት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እንደሚሠራም ጠቅሰዋል፡፡
ከደቡብ ወሎ ዞን መካነ ሰላም ወረዳ የመጡት አቶ ሀሰን አስፋው የወረዳው የመጠጥ ውኃ ችግር ሰፊ ነው፤ ማሕበረሰቡ ውኃ የሚያገኘው በ15 ቀን አንድ ቀን ነው ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የወረዳውን የውኃ ችግር ይቀርፋል፤ ማሕበረሰቡም ግንባታውን ለማገዝ 14 ሚሊዮን ብር ወጭ በማድረግ 17 ሄክታር መሬት ከሦስተኛ ወገን ነፃ አድርጓል፤ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ድርሻ ያደርጋል ብለዋል፡፡
በዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሰኃላ ሰየምት ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሚሶ ፈንታሁን ለረጅም ዓመታት ወረዳዋ የውኃ ችግር አጋጥሟታል ቆይቷል፤ ይህም ማሕበረሰቡን ለቅሬታ ዳርጎ ነበር ብለዋል፡፡ አሁን የሚገበባው የውኃ ፕሮጀክት ችግሩ እንዲፈታ አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ: ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleመተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ ታኅሣሥ 13/ 2013 ዓ.ም. በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 207 መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።
Next articleየሀገር መከላከያ ሠራዊት ትህነግን በማስወገድ ያስመዘገበውን ድል በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩትን ግድያዎች በማስቆም ሊደግም እንደሚገባ የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡