
መተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ ታኅሣሥ 13/ 2013 ዓ.ም. በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 207 መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 17/2013 ዓ.ም (አብመድ)
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ ታኅሣሥ 13/ 2013 ዓ.ም. ከለሊቱ 10፡00 ሰዓት በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 207 መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረገው ክትትል አረጋግጧል።
ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው የቡለን ከተማ ነዋሪዎች፣ ምስክሮች፣ ተጎጂዎችና በመጀመሪያ እርዳታ አቅርቦት የሚሳተፉ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪዎች፣ እስከ ታኅሣሥ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር በተደረገ የአስከሬን ፍለጋ፣ የሟቾች ቁጥር 207 መድረሱን አስረድተዋል።
የሟቾችን ማንነት የማጣራቱ ስራ በመታወቂያና ከጥቃቱ በተረፉ ሰዎች ምስክርነት አማካኝነት መጀመሩ ታውቋል። ፖለስ እና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ጨምሮ የምርመራ ኮሚቴው የሟቾቹን ማንነት የማጣራት፣ የመመዝገብና አስከሬን የመቅበር ተግባራትን እየተከታተለ ይገኛል ብሏል ኢሰመኮ።
በዚህም መሰረት፣ በጥቃቱ ሕይወታቸው ካለፉ አዋቂዎች መካከል 133ቱ ወንዶች ሲሆኑ 35ቱ ሴቶች ናቸው። አንድ የስድስት ወር ሕጻንን ጨምሮ በጥቃቱ አስራ ሰባት ሕጻናት ተገድለዋል። ቀሪ ሃያዎቹ አዛውንቶች መሆናቸው ተረጋግጧል።
ከሟቾች መካከል ሁለቱ በቡለን ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እያለ ታኅሣሥ 15 /2013 ዓ.ም. የሞቱ መሆናቸውን፣ ኮሚሽኑ በቡለን ከተማ ካሉ የሥራ ኀላፊ ተረድቷል።
በቡለን ወረዳ ከሚገኙ አራት ቀበሌዎች (ጭላንቆ፣ በኩጂ፣ ዲሽባኮ እና ባር) የተፈናቀሉና ቁጥራቸው ከ500 የሚበልጡ ሰዎች በጋሌሳ ቀበሌ በሚገኝ የአውቶቡስ መናኃሪያ ተጠልለው ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅት መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን የሚያሟላ እርዳታ የሚያገኙት ከአካባቢው ነዋሪ መሆኑን ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው አንድ ተፈናቃይ አስረድተዋል።
በተመሳሳይ መልኩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቀበሌውን ጥለው ከ40 ኪ.ሜ. በላይ በእግራቸው በመጓዝ ወደ ቡለን ከተማ በመግባት ላይ ይገኛሉ። በከተማው በሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና አንድ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ግቢ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ተጠልለዋል።
የቡለን ከተማ ነዋሪዎች እና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተፈናቃዮችን እየመገቡ ቢሆንም ወደ ቀዬአቸው እስከሚመለሱ ድረስ የሚቆይ አፋጣኝ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተመልክቷል።
‹‹የቡለን ከተማ ተጥለቅልቋል። ወደ ከተማው ከገጠር ከተማ የሚያመሩ መንገዶች አሁንም ከብቶቻቸውን እየነዱ በሚሰደዱ ሰዎች ተሞልተዋል›› ሲሉ አንድ የአይን እማኝ የሆኑ የቡለን ነዋሪ ለኢሰመኮ ተናግረዋል።
ስለሆነም፣ ኢሰመኮ ተፈናቃዮችና ተጎጂዎች በሰብአዊ እርዳታ እጥረት ምክንያት ለተጨማሪ አደጋ እንዳይጋለጡ ለመከላከል የሚመለከታቸው ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ በድጋሚ ያሳስባል ነው ያለው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የአስከሬን ፍለጋና የመቅበር ሥነ ሥርዓቱ ሰብአዊ ክብርን በጠበቀ መልኩ እንዲሆን ጥሪ አቅርቧል።
የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ለመመለስ እንዲሁም አጥፊዎችን ከሕግ ፊት የማቅረብ ሂደቱ መጀመሩንና ይህንኑ በተመለከተ ከመንግስት የሚሰጡ መረጃዎችን ኮሚሽኑ መመልከቱን ገልጿል።
የክልሉን የፀጥታ መዋቅር እና ኃይል ለማጠናከር የተወሰዱ ርምጃዎች አበረታች ቢሆኑም ርምጃዎቹ የሰብአዊ መብቶችን ጥበቃና የሲቪል ሰዎችን ደኅንነት ያገናዘቡ መሆን እንዳለባቸው ባወጣው መግለጫ አሳስቧል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ