“ሞትንና ቀውስን የሚደግሱልንን ለመመከት በጋራ ልንቆም ይገባል” ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ

167
“ሞትንና ቀውስን የሚደግሱልንን ለመመከት በጋራ ልንቆም ይገባል” ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 17/2013 ዓ.ም (አብመድ) “ሞትንና ቀውስን የሚደግሱልን እንዳሉ አይተናል፤ የምናየውና የምንሰማው አሰቃቂ ሆኖ ዳርቻ አልባ በመሆኑ ችግሩን ለመመከት በጋራ ልንቆም ይገባል” ሲሉ ፕሬዚዳት ሣህለወርቅ ዘውዴ ጥሪ አቀረቡ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 4 ሺህ 87 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል። በመርሃ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ለተመራቂ ተማሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት “ኢትዮጵያን ነገ የምትመሯት የዛሬ ተመራቂዎች ናችሁ” ብለዋል።
በመልዕክታቸው “የምታኮራና ተስፋ ያላት ሀገር ብትኖረንም ብዙ ፈተናዎች ተደቅነውብናል” ነው ያሉት። አሁን እየተጋፈጥናቸው ያሉ ችግሮች የተለያዩና ልዩ ትኩረትን የሚሹ ናቸው ብለዋል።
ምክንያቱ ደግሞ በአንድነታችን፣ በሉአላዊነታችን፣ በአብሮነታችን፣ በህልውናችን፣ በዜጎች የህይወት መኖር መብት ላይ ችግር አነጣጥሮብናል ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቷ ለፖለቲካ ፍጆታና ለቡድን ጥቅም ሲባል በእሳት መጫወት አደጋው የከፋ መሆኑን አስገንዝበው፤ “ካልተጠነቀቁ ሰደድ እሳት ይሆናል” ብለዋል። “ሞትንና ቀውስን የሚደግሱልን እንዳሉ አይተናል፤ የማይፈነቅሉትም ድንጋይ ባለመኖሩ ችግሩን ለመመከት በጋራ ልንቆም ይገባል” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
“ዜጎች በሀገራቸው መፈናቀል፣ መንከራተት፣ መጨፍጨፍ፣ መሸማቀቅ የለባቸውም” ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ትውልዱ ኢሰብአዊነትን የሚታገልና ሞት የሚደግሱ አካላትን በዝምታ የማያልፍ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል።
“አሁን ኢትዮጵያ ሁሉንም ልጆቿን የምትሻበት ጊዜ በመሆኑ የሕዝቦቿን ሰላም መንሳት፤ መግደልና ማፈናቀል አይፈቀድም የሚል ትውልድ ሁኑ” ሲሉ ለተመራቂዎቹ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ኢዜአ እንደዘገበው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የፌዴራል መንግሥት የአማራ ሕዝብ ቁስል ሊያመው ይገባል”
Next articleመተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ ታኅሣሥ 13/ 2013 ዓ.ም. በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 207 መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።