
“የፌዴራል መንግሥት የአማራ ሕዝብ ቁስል ሊያመው ይገባል”
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 17/2013 ዓ.ም (አብመድ) የፌዴራል መንግሥት የሕዝብን ሠላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባ አማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የጸጥታ ዘርፍ አማካሪ ጠየቁ። በምክትል ቢሮ ኃላፊ ደረጃ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የጸጥታ ዘርፍ አማካሪ ከፋለ እሱባለው በመተከል ዞን በንጹሃን ላይ ማንነትን መሠረት አድርጎ የሚካሄደውን ጭፍጨፋ አስመልክቶ ከአብመድ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአማራ፣ የአገው የጉሙዝ፣ የበርታ፣ የኦሮሞ፣ የሺናሻ እና ሌሎችም ብሔሮች ብዝኀነትን አቻችለው በመኖር የረጅም ዘመናት ልምድ እንዳላቸው ተናግረዋል። በተለይ ክልል ሆኖ ከመመስረቱ በፊት ሰፊ ብዝኀነትን ያስተናግድ የነበረ ቀጠና መሆኑንና በአብሮነት የመኖር እሴት ጠንካራ እንደነበር ተናግረዋል።
ለከተሜነት መስፋፋትና ለክልሉ ሁለንተናዊ እድገት የእነዚህ ሕዝቦች ሚና በጉልህ የሚነሳ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ከተመሠረተ ጀምሮ አማራ ጠል ኀይሎች ባዘጋጁት ሀሰተኛ ትርክት ምክንያት በተለይ በአማራ ሕዝብ ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት፣ ግድያ፣ መፈናቀልና ዝርፊያ በመፈጸም ላይ ነው ብለዋል፡፡
ግድያውና ጭፍጨፋው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ያሉት የጸጥታ ዘርፍ አማካሪው አቶ ከፋለ በተለይ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በከፍተኛ ደረጃ በተደራጀ መልኩ እየተፈጸመ መሆኑን አስታውቀዋል።
ግድያዎች ሲፈጸሙ ታቅደው በመሆኑ እስካሁን በመረጃ ያልተያዙ በርካታ ዘር ተኮር ግድያዎች መፈጸማቸውን አመላክተዋል። ሞተው ጫካ ውስጥ የሚገኙ፣ የሚቀበሩና መረጃቸው ያልተገኙ እንዳሉም ገልጸዋል።
ዘር ተለይቶ ንጹኀን ሰዎች ተጨፍጭፈዋል፤ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ ሰብሎችና ቤቶችም ተቃጥለዋል፣ ሰዎችም ከባለጸጋነት ወደ ድህነት ተቀይረዋል፤ ለዚህ ሁሉ ችግር ምክንያቱ በኢንቨስትመንት ስም በሕዝቡ ውስጥ ተሰግስገው ጸረ አማራና ጸረ አገው እንቅስቃሴ የሚያደረጉ ኀይሎች መኖራቸው፣ በጸረ አማራነት የተሰነደው በአማራ ላይ የተዛባ ትርክት መሰራጨቱና ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበ ሕገመንግስት በክልሉ መዘጋጀቱ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
እስከቅርብ ጊዜ ድረስም በመተከል ዞን በሚኖር የአማራ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ የሽብርና የግድያ ወንጀሎች ተፈጽመዋል ብለዋል። ችግሩ የአካባቢውን ሕዝብ የማይወክል በመሆኑ ከማኅበረሰቡ እሴት የሚመነጭም አይደለም ብለዋል። አብሮ መኖር፣ አብሮ መብላት፣ መጠጣትና መደሰት የጉምዝ ማሕበረሰብ በገለጫ ነው፤ አንዳንዶችም በአማራ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ተጋፍጠው መስዋዕትነት የከፈሉ ጉምዞች፣ በቤታቸው አስጠልለው ከጉዳት የታደጉ የቀበሌ ሠራተኞች መኖራቸውን ተናግረዋል።
በአካባቢው እየተፈጸመ ላለው ጭፍጨፋም በማሕበረሰቡ ውስጥ የተሳሳተ ትርክት የሚረጩ ኀይሎች፣ አጀንዳ ተሰጥቷቸው የሚንቀሳቀሱ ጥቅመኛ የመንግሥት አመራሮች እና በመግደልና በማፈናቀል የሚያምኑ የከሰረ ፖለቲካ አራማጆች ተጠያቂዎች ናቸው ብለዋል።
በአካባቢው የሚታዩ ችግሮችን እልባት ለመስጠት በመከላከያ ሠራዊት የሚመራ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ የሦስት ወራት እቅድ ቢወጣም የሚፈለገው ለውጥ አልተገኘም። ከክልሉ አመራር በቂ እገዛ አለመደረጉ ይልቁንም አመራሩ የማይገባ አካሄድን በመከተሉ መከላከያን አላስፈላጊ መስዋዕትነት እያስከፈለ እንደሚገኝ አብራርተዋል። ማሕበራዊ መሠረቱ ምቹ አለመሆኑ፣ እጃቸው ያልጠራ የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት መኖራቸውም ኮማንድ ፖስቱ ውጤታማ ሥራ እንዳይሠራ ማድረጉን አንስተዋል።
በሌላ በኩል የፌዴራል መንግሥቱ ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት፣ የኀይል ሥምሪቱ እና የሎጂስቲክስ ሁኔታው በጣም ዝቅተኛ መሆኑን አስታውቀዋል። በተለይ ሰላም ሚኒስቴር ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ መሆኑን በመግለጽም በተደራጀበት አግባብ ሕዝቡን ከሞት እየታደገ አለመሆኑን ጠቅሰዋል።
ጉዳዩ አሳሳቢ ከመሆኑ አኳያ የተለየ ፖለቲካዊ ትርጉም ሊሰጠው ይገባ እንደነበርም ተናግረዋል።
አንድና ሁለት ሰው በማሠር መፍትሄ አይመጣም ያሉት አቶ ከፋለ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መሠረታዊ ለውጥ ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል። በአካባቢው ያሉ ብሔረሰቦችም በሰላም መኖር እንደሚጠቅም ተገንዝበው እየተጨፈጨፈ ላለው ሕዝብ ድምጻቸውን ሊያሰሙ ይገባል ብለዋል።
“የፌዴራል መንግሥት የአማራ ሕዝብ ቁስል ሊያመው ይገባል!” ያሉት አማካሪው በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶችም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጉዳዩን አጀንዳቸው ሊያደርጉት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የመገናኛ ብዙኀን በንጹሃን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጭፍጨፋ በተገቢው መልኩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እያድሱ አይደለም ያሉት አቶ ከፋለ ይህም ሊስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ኀላፉነታውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ