
“ሰባት ልጆቼ ተገደሉብኝ፣ በኢትዮጵያ ምድር እንዲህ ዓይነት ግፍ ይፈጸማል ብየ አስቤ አላውቅም” ከግድያው የተረፉ ተፈናቃይ እናት።
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 17/2013 ዓ.ም (አብመድ) ወይዘሮ ደስታ ተበጀ በድባጤ ወረዳ ከ42 ዓመታት በላይ ስምንት ልጆችን ወልደው ኖረዋል። ጥቅምት 01/2013 ዓ.ም ከለሊቱ ሰባት ሰዓት ግን የመርዶ ቀን ሆነባቸው። በዚህ ዕለት የተደራጁ እና የታጠቁ ኅይሎች አስከፊውን ጭፍጨፋ እንዳደረሱባቸው ነግረውናል። “ብቻየን አስቀሩኝ” ያሉት ወይዘሮ ደስታ ማቅ ለብሰው ከስምንት ልጆቻቸው ሰባቱ ተገድለውባቸው አንድ ልጃቸውን ብቻ ይዘው በቻግኒ ከተማ በጊዚያዊነት ተጠልለው ይገኛሉ። “በኢትዮጵያ ምድር እንዲህ ዓይነት ግፍ ይፈፀማል ብየ አስቤ አላውቅም ነበር” ብለዋል ተጎጂዋ እናት።
ከድባጤ ወረዳ የተፈናቀሉት አቶ አለሙ በየነ ” ባለቤቴንና ልጆቸን አጥቻለው፤ ቤቴ ፈርሷል፤ ከባድ ችግር ውስጥ ነው ያለውት” ብለዋል፡፡ አቶ አለሙ ግድያው የተፈፀመው በነዋሪው ሳይሆን በክልሉ መንግሥት የተወሰኑ አመራሮች ስልጠና በወሰዱ ኀይሎች መሆኑንም ተናግረዋል።
ሌላው ተፈናቃይ ሞላ በሪሁን ግፍ ፈፃሚዎች ለሊት ዘጠኝ ሰዓት ቤት ሰብረው በመግባት አራት ቤተሰባቸውን እንደገደሉባቸው በኀዘን ውስጥ ሆነው ነግረውናል። ግድያ እና የንብረት ቃጠሎ ከመድረሱ በፊት ለሚመለከተው አካል መረጃ ቢያደርሱም የተሳሳተ መረጃ ነው በማለት ሰሚ እንዳለገኙ ጠቅሰዋል። ጭፍጨፋው በጅምላ ዘር ማጥፋት እንደሆነም ተናግረዋል።
ወጣት እሱባለው ደጉ ደግሞ ከቻግኒ ከተማ ቆይቶ ወደ ድባጤ ለመሄድ በተሳፈረበት መኪና በደረሰው ጥቃት 60 ሰዎች ሲገደሉ እሱ ሙቷል ተብሎ ሕይወቱ መትረፉንና በዕለቱ ዘግናኝ ጭፍጨፋ መፈጸሙን ነው ያስረዳን።
በአሁኑ ወቅትም የቻግኒ ከተማ ሕዝብ እና አስተዳደር የነፃ ህክምና አግልግሎት በመስጠትና ማረፊያ ድንኳን በማዘጋጀት ለእሱና ለሌሎች ለተፈናቃዮች እንክብካቤ እያደረጉላቸው መሆኑን ተናግሯል፡፡
ዘጋቢ:- አዳሙ ሽባባው ከቻግኒ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ