የአላማጣ ከተማ ሰላማዊና የተረጋጋች መሆኗን ጊዜያዊ አስተዳደሩ አስታወቀ።

423
የአላማጣ ከተማ ሰላማዊና የተረጋጋች መሆኗን ጊዜያዊ አስተዳደሩ አስታወቀ።
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 16/2013 ዓ.ም (አብመድ) በቅርቡ ከወራሪው፣ ተስፋፊውና አሸባሪው ትህነግ ነፃ የወጣቸው አላማጣ ከተማ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መሆኗን ጊዜያዊ አስተዳደሩ አስታውቋል። የአላማጣ ከተማ ጊዜያዊ ከንቲባ ካሳ ረዳ በተለይም ለአብመድ እንዳሉት ከተማዋ ከትህነግ ቀንበር ስትላቀቅ በመጀመሪያዎቹ ቀናት ያለመረጋጋት ችግር እንደነበር አስታውሰዋል።
የአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻና የከተማዋ ሕዝብ በጋራ በሠሩት ሥራ ለከተማዋ ሥጋት የነበሩ የትህነግ ተላላኪዎችን በቁጥጥር ሥር የማዋል፣ ትጥቅ የማስፈታትና ከተማዋን በአፋጣኝ የማረጋጋት ስራ መሰራቱንም ተናግረዋል። ከተማዋ አሁን ላይ ሰላማዊና የተረጋጋች መሆኗንም ጊዜያዊ ከንቲባው አስታውቀዋል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፀጥታ ኀይሉ ጋር በመሆን ከተማዋን ካረጋጋ በኋላ ነዋሪዎች መደበኛ እንቅስቃሴያቸውን እንዲጀምሩና አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ መደረጉንም አስታውቀዋል።
ከአሁን በፊት የአላማጣ ወጣት በነፃነት የመንቀሳቀስ እድል እንዳልነበረው የተናገሩት አቶ ካሳ አሁን ላይ ስቃይ ሲደርስበት የነበረው ወጣትም ሠላሙን አረጋግጧል ብለዋል፡፡ ጊዜያዊ ከንቲባው የተገኜውን ሰላም በአግባቡ በመጠቀም የሕዝቡን ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመፍታት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ትህነግ በከተማዋ የነበሩ አብዛኛዎቹን ተቋማት በማፍረሱ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በማፅዳትና በማስተካከል ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ ማድረጉንም አስረድተዋል።
ትህነግ መረጃ ለመደበቅና ሀብቱ የራያ ሕዝብ በመሆኑ ተጠቃሚ እንዳይሆን ለማድረግ ተቋማትን ማውደሙንም አቶ ካሳ ተናግረዋል። ወራሪው፣ ተስፋፊውና አሸባሪው ትህነግ ሲፈረጥጥ ጥሏቸው የሸሹ ጠቃሚ መረጃዎችን በተቻለ መጠን የመሰብሰብ ሥራ መሰራቱንም አስታውቀዋል። ማንነቱ ታፍኖ ይኖር የነበረውን ማኅበረሰብ ሥነ ልቦና የመጠገንና የፀጥታውን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ሥራዎች መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
የተገኜውን ለውጥ በመጠቅም የተጎዳውን ሕዝብ መካስ የሚያስችል አገልግሎት በመስጠት እንሰራለንም ብለዋል ጊዜያዊ ከንቲባው ካሳ ረዳ። አሁን ላይ አደራ የተጣለበት የራያ ጊዜያዊ አስተዳደር ሁሉ የሕዝብን ጥያቄ መለየት፣ ማወቅና መመለስ ይገባዋልም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበሰላም ቀን ማረስ ፣ በክፉ ቀን የወገን አለኝታነቱ የቆዬ መገለጫ ነው። ጀግና ሲተኩስ ብቻ ሳይሆን ሲራመድም ያስፈራል። ልቡ ሸፍቶ ከቤት ሲወጣ ፊቱ ባሻገር ይጋረፋል።
Next article“ሰባት ልጆቼ ተገደሉብኝ፣ በኢትዮጵያ ምድር እንዲህ ዓይነት ግፍ ይፈጸማል ብየ አስቤ አላውቅም” ከግድያው የተረፉ ተፈናቃይ እናት።